ኢሳት (መጋቢት 20 ፥ 2008)
ባለፈው አመት ሃምሌ ወር የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ወቅት ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር ያደረጓቸውን ውይይቶች የሚከታተል ከፍተኛ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሃላፊ ወደ አዲስ አበባ እንደሚጓዙ ተገለጠ።
ይኸው በአሜሪካው ረዳት የውጭ፣ የዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ሚኒስትሩ ቶም ማሊኖውስኪ የሚመራው የልዑካን ቡድን ማክሰኞ ወደ አዲስ አበባ እንደሚገባ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል።
በኢትዮጵያ ቆይታቸውም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሃላፊው ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር በመገናኘት በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ የሚከሩ ሲሆን ይህም ጉብኝት ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ባለፈው አመት ሃምሌ ወር ካደረጉት ጉብኝት ጋር ግንኙነት ያለው እንደሆነ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በአዲስ አበባ ቆይታቸው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በሃገሪቱ ያለው የሰብዓዊ መብት አያያዝ እና የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት እንዲሻሻል ይፋዊ ጥረት ማቅረባቸው ይታወሳል።
በሃገሪቱ ወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያን ሰጥተው የነበሩ ፕሬዚደንቱ በሃገሪቱ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶችና አመራሮች እንዲሁም የመገናኛ ብዙሃን በነጻነት የመንቀሳቀስ መብታቸው መከበር እንዳለበት አሳስበው እንደነበር ይታወቃል።
“አንድ ሃገር ስኬታማ ልትሆን የምትችለው የሃገሪቱ ዜጎች በሃገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ስለመሳተፋቸው ሲያውቁና ሲያረጋግጡ ብቻ ነው” በማለት ባራክ ኦባማ በወቅቱ ገልጿል።
ፕሬዚዳንቱ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር ያደረጓቸውን ውይይቶችና በሁለት ሃገራት መካከል ስጋት ናቸው ተብለው የተነሱ ጉዳዮችን ለመከታተልም የአሜሪካው ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶችና የዴሞክራሲ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ሰፊ ውይይትን እንደሚያካሄዱ ለመረዳት ተችሏል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከኢትዮጵያ ቆይታቸው በኋላ አሜሪካ በተደጋጋሚ በሰብዓዊ መብት ዙሪያ ቅሬታዋን በምታቀርባቸው ሩዋንዳ፣ ብሩንዲና ኬንያ ተመሳሳይ ጉብኝት እንደሚያደርጉም ታውቋል።
የአሜርካ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አራተኛ ወሩን በዘለቀው የኦሮሚያ ክልል ተቋውሞ ለሁለተኛ ጊዜ ስጋቱን በመግለጽ የኢትዮጵያ መንግስት ለተቃውሞ ሰላማዊ እልባት እንዲሻ መጠየቁም የሚታወስ ነው።
በሃገሪቱ የሚነሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ሌሎች ተጓዳኝ ሃገራዊ ጉዳዮች በሁለቱ ወገኖች መካከል ውይይት ይካሄድባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።