ኢሳት (መጋቢት 22 ፥ 2008)
በኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ለመመልከትና ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር ለመምከር ወደኢትዮጵያ የተጓዘው የአሜሪካ መንግስት ከፍተኛ ልዑካን በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ያሉ ግጭቶችን ጨምሮ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ባለው የሰብዓዊ መብት ይዞታ ላይ የኢትዮጵያ መንግስት ማብራሪያ ጠየቁ።
በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዲሞራሲያ የሰብዓዊ መብቶች ረዳት ሚኒስቴር ቶም ማሊኖዊስኪ በኢትዮጵያ ከሚገኙ የአሜሪካ አምባሳደር ፓትሪሺያ ሃስላክ ጋር በመሆን፣ ከኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ጋር በሰብዓዊ መብትና በመልካም አስተዳደር ዙሪያ መወያየታቸው ታውቋል።
በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኢምባሲ ይፋ ባደረገው ሪፖርት መሰረት የአሜሪካ ልዕካን በበርካታ ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ ከመንግስት ሃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።
የኢትዮጵያን መንግስት በመወከል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ በአቶ ታየ አጽቀስላሴ የተመራ ቡድን ከአሜሪካው ልዑካን ጋር በተወያየበት ወቅት በምርጫ 2007 ሂደቱና ውጤቱ እንዲሁም የኦሮሚያ ህዝባዊ እንቅስቃሴ በአማራ ክልል የተከሰቱ ግጭቶች ተነስተዋል።
በኢትዮጵያ የሲቪክ ድርጅቶቹ ሚና መገደብ፣ የመገናኛ ብዙሃን ምህዳር መጥበብ የውይይት ርዕስ መሆናቸውም ተመልክቷል።
በኢትዮጵያ መንግስት ተወካዮች የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አመታዊ ሪፖርት እንዲሁም አርበኞች ግንቦት ሰባትን በተመለከተ ጥያቄ ማንሳታቸውንም መረዳት ተችሏል።