የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ የኢትዮጵያ ጉብኝት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተቃወሙት

ሰኔ ፴ (ሠላሳ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በዓለማቀፍ ታላላቅ የመገኛኛ ብዙሃን አውታሮች መነጋገሪያ ሆኖ የዘለቀው የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ኢትዮጵያን የመጐብኘት ውጥን አሜሪካ አምባገነን መንግስታትን ከመደገፍ የመነጨ በመሆኑ እምብዛም ትኩረት የሚሠጠው ጉዳይ አይደለም ብለዋል የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሣይንስ መምህር እና የመድረክ የፖለቲካ ማህበር አመራር ዶ/ር መረራ ጉዲና ´´አሜሪካ አምባገነኖችን የምትደግፍም ሃገር መሆኗን በምሳሌ አስደግፎ ማስረዳት ይቻላል ይላሉ፡፡ በቀዝቃዛው ጦርነት ጊዜ “የኛ ወዳጅ ነው” እያሉ የአፍሪካ ቁጥር አንድ አምባገነን የነበረውን ሞቦቱ ሴሴኮን እና ሌሎች ነፍሰ ገዳይ የነበሩ መሪዎችን ለራሷ ጥቅም ስትል ስትደግፍ ኖራለች፤ የፕሬዚዳንቱ ጉብኝትም የተለየ አንድምታ የለውም፤ የዚሁ ፖሊሲም ውጤት ነው“ ብለዋል።
´´የኔ አሽከሮች እስከሆኑ ድረስ ምንም ቢያደርጉ ሆዴ አይጨክንባቸውም” የሚል ፖሊሲ ሃገሪቱ አላት” ያሉት ዶ/ር መረራ “እናሸንፋለን ብለው የገቡበት የሽብር ትግል አቅጣጫውን ቀይሮ እየሰፋ መምጣቱ ለጭንቀት ዳርጓቸው ጉዳይ አስፈፃሚ ሃገራትን እንዲንከባከቡ አስገድዷቸዋል” ሲሉ አክለዋል፡፡
“ዲሞክራሲ እንደሸቀጥ እቃ ከውጪ ተገዝቶ የሚመጣና የሚሸጥ አይደለም የሚሉት ዶ/ሩ፤ “የኢትዮጵያ ህዝብ ከሚያደርገው ትግል የሚመጣ በመሆኑ አንድ የአሜሪካ መሪ ዲሞክራሲያዊ ያልሆነ ሀገርን ስለጐበኘ የትግሉ ተዋናዮች ተስፋ መቁረጥ የለባቸውም ´´ሲሉም አሳስበዋል፡፡
በአሜሪካ ይደግፍ የነበረው የአፄ ኃይለሥላሴ ስርአትም ሆነ በሶቪየቶች ይደገፍ የነበረው የደርግ ስርአት መውደቁን ያስታወሱት ዶ/ር መረራ፤ ይሄም ስርአት ሃቀኛ ዲሞክራሲ ስለማስፈኑ የኦባማ ጉብኝት ማረጋገጫ አይሆንም፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ትግልንም አያዛንፈውም ሲሉ አክለዋል።
“ኦባማ ኢትዮጵያን በዚህ ሁኔታ መጐብኘት ለአሜሪካ ህዝብ አሣፋሪ ነው” ያሉት ዶ/ር መረራ በአንፃሩ የኢትዮጵያን ህዝብ ትግል የሚገታው አይሆንም ብለዋል፡፡ ኦባማ ወደ ስልጣን ሲመጣ አምባገነኖች ቦታ አይኖራቸውም እያለ ስለዲሞክራሲ የሚዘምር የነበረና የወጣቶችን ቀልብ መግዛት የቻለ ነበር የሚሉት ዶ/ሩ በመጨረሻ በዚህ ደረጃ መውረዱ ቃሉን እንደበላ ነው የሚያረጋግጠው ሲሉ ትችታቸውን ሰንዝረዋል፡፡
የመላ ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፕሬዚዳንት አቶ አበባው መሀሪ በበኩላቸው ´´የኢትዮጵያ መንግስት እየፈፀመ ያለውን የዲሞክራሲያዊ መብቶችና ሰብአዊ መብት ጥሰቶችን እንዲያርም የሚያሣስቡ ከሆነ ጉብኝቱ አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል፤ ዝም ብሎ በፀረ ሽብር ጉዳይ ላይ ተወያይቶ የሚመለሱ ከሆነ ትክክል አይሆንም´´ ብለዋል፡፡

የሠማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊው ዮናታን ተስፋዬ በበኩሉ፤ “የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ወደ ኢትዮጵያ መምጣት በፓርቲው በኩል ብዙም ትኩረት የሚሠጠው አይደለም” ያለ ሲሆን፣ “ድሮም አሜሪካ አምባገነኖችን ትረዳ ነበር አሁንም እየረዳች ነው፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ላለው አፈናና ጭቆናም አንደኛዋ ተባባሪ አሜሪካ ስለሆነች ህዝቡም ያን ያህል ትኩረት የሚሰጠው አይመስለኝም” ሲል አስተያየቱን ገልጿል፡፡
የአሜሪካው 44ኛ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በኢትዮ-አሜሪካ የ112 አመታት የዲፕሊማሲ ታሪክ ውስጥ ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ማቀዳቸው መነጋገሪያ ሆኖ የከረመ ሲሆን ዋሽንግተን ፖስት እና ዘ ጋርዲያን ጋዜጦችን እቅዱን ክፉበኛ አብጠልጥለውታል ሲል አዲስ አድማስ ጋዜጣ ዘግቧል።