ኢሳት (ሰኔ 22 ፥ 2009)
የአሜሪካው ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰኞ በወሰነው መሰረት በአብዛኛው የእስልምና እምነት ተከታዩች ካሉባቸው ስድስት አገሮች የሚመጡ ጎብኝዎች እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ከሰኔ 29/2017 ምሽጥ 8 ሰአት ጀምሮ ወደ አገሪቱ መግባት እንደማይችሉ የውጭ ጉዳይ መ/ቤት አስታወቀ።
ጎብኚዎቹ አሜሪካ የሚኖሩ የቅርብ ዘመድ ከሌላቸው ወይንም በአሜሪካ ከሚገኝ ድርጅት እና የትምህርት ተቋም ጋር የስራ ስምምነት ከሌላቸው ወደ ሃገሪቱ መግባት አይችሉም።
የውጪ ጉዳይ መ/ቤቱ አዲሱን መመሪያ ያወጣው ሰኞ እለት የአሜሪካው ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከስድስት አገራት በሚመጡ ዜጎች ላይ ለመጣል ካወጡት መመሪያ ውስጥ የተወሰነው ክፍል ተግባራዊ እንዲሆን በወሰነው መሰረት ነው።
ከስድስቱ አገራት ማለትም ከኢራን፣ ሊቢያ፣ ሶማልያ፣ ሱዳን፣ ሶሪያ እና የመን የሚመጡ ዜጎች አሜሪካ የሚኖሩ የቅርብ ቤተሰብ ወይም ዘመድ ከሌላቸው ወይም አሜሪካ ከሚኖር ድርጅት ጋር የስራ ስምምነት ካላደረጉ እንዲሁም ከትምህርት ተቋማት ጋር የስራ ወይንም የትምህርት ግንኙነት ከሌላቸው ከሃሙስ ማታ ጀምሮ ወደ አገሪቱ መግባት እንደማይችሉ መመሪያው ሲያሳውቅ የዝምድና እና ግንኙነትን በተመለከተም የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ በላከው ማብራሪያ ወላጆች የትዳር አጋር፣ ልጅ፣ የእህት ወይም የወንድም ልጅ፣ ወንድም፣ እህት፣ እንጀራ አባትና እናት በኩል ካለ የቤተሰብ ግንኙነት ውጪ ሌሎች ዘመዶችን ይከለክላል።
መመሪያው ኣያቶችን፣ የልጅ ልጆችን፣ የአክስት ወይንም የአጎት ልጆችን፣ የወንድም ወይም የእህት የትዳር አጋሮችን እንዲሁም እጮኛን መከልከሉ በተለያዩ አካላት ዘንድ ቁጣን ቀስቅሷል።
የሙስሊሞች የመብት ተቆርቋሪ ድርጅት የህግ መምሪያ ሃላፊ ጆናታን ስሚዝ ለዋሽንግተን ፖስት እንደተናገሩት የዝምድና ግንኙነትን በተመለከተ አያቶችን፣ የአክስትና የአጎት ልጆችንና ሌሎች የቤተ ዘምድ አባላትን መመሪያው መከልከሉ ግራ የሚያጋባና በተለምዶ ያለን የቤተሰብ ዝምድና ትስስርን የማያንጸባርቅ ብለውታል።
በስደተኞች ጉዳይ ላይ ብዛት ያላቸው መጽሃፍትን በመድረስ የሚታወቁት የኮርኔል ዩንቨርስቲ የህግ ፕሮፌሰር ስቲፈን ዬልሎኸር በበኩላቸው በአሜሪካ ከሚገኙ ስደተኞች ውስጥ ከግማሽ በላይ ያህሉ ቅርብ የሆነ የቤተሰብ አባል የሌላቸው ሲሆን “የጠፉት የሱዳን ልጆች” በመባል የሚታወቁትና በረሃብና በጦርነት ምክንያት በጉዲፈቻ የሚመጡ ልጆች የአዲሱ መመሪያ ሰለባ ይሆናሉ ብለዋል።
በእንጀራ አባትና እናት በኩል ላሉ ወንድምና እህት የፈቀደ መመሪያ ለምን አያቶችን ይከላከላል ሲሉም ተችተው ሽብርተኞችን ለመከላከል የወጣው መመሪያ ሌሎች ሰላማዊ ሰዎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ መከልከል ስለሌበት የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አስገንዝበዋል።
መመሪያው ቤተሰቦችን በዚህ መልክ መነጠሉ ርሕራሄ የጎደልው ተግባር ነው ያሉት ደግሞ በአሜሪካ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዳሬክተር ናውሪን ሻህ ናቸው። መመሪያው ቀድሞውንም የፕሬዝደንት ትራንምፕ ሕግ ጭካኔና አድሎዊነት የተሞላበት መሆኑ ማስረጃ ነው ብለዋል። ድርጅታቸውም በኒዮርክ፣ በዋሽንግተን ዲሲ እንዲሁም በሎሳ አንጀለስ ባሉ ኤርፖርቶች ጉዳዩን እንደሚከታተለው ተናግረዋል።
ሰኞ በጠቅላይ ፍ/ቤት የወጣው ሕግ አፈፃፀሙ እስከ ሐሙስ ድረስ የቆየው በጉዞ ላይ ያሉ ሰዎችን መስተጓጎል ለማስወገድና ከዚህ ቀደም የፕሬዝደንት ትራምፕ እገዳ ተፈጻሚ በሆኑባቸው የመጀመርያ ቀናት የተፈጠረውን ትርምስ ለማስቀረት መሆኑ ተጠቁሟል።
ውሳኔው በተለያዩ ሀገራት ከሚገኙ የስደተኛ ጣቢያዎች የሚመጡትንም የሚያሰናክል ቢሆንም ለዚህ ዓመት ኮታ ከተመደበው 50,000 ስደተኞች ውስጥ እስከ ረቡዕ ድረስ 49,008 መግባታቸውን ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል።