የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ለተፈጠረው ችግር መፍትሄው ነጻነትን ማስፋትእና ሁሉን አቀፍ ውይይት መደረግ ሲችል ነው አሉ
(ኢሳት ዜና የካቲት 29 ቀን 2010 ዓ/ም) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቲሊርሰን እንዳሉት በኢትዮጵያ እየተደረገ ያለውን ስልጣንን የማሸጋገር ሂደት እንደግፈዋለን ያሉት ባለስልጣኑ፣ አሜሪካ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በጥብቅ መቃወሙዋንም ገልጸዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የዜጎችን መብት እንደሚገድብ በተለይም ሃሳብን የመግለጽ ነጻነትን እንደሚያፍን ለኢትዮጵያ ባለስልጣናት እንደገለጹላቸው ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የጸጥታ ሃይሎች ጸጥታ በሚያስከብሩበት ወቅት የሰዎችን መብት እንዲያክብሩና አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ለኢትዮጵያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ወርቅነህ ገበየሁ እንደገለጹላቸው የተናገሩት ቲሊሪሰን፣ “የዲሞክራሲ ለውጥ የሚመጣው፣ የኢኮኖሚ እድገት የሚኖረውና ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት የሚፈጠረው ፣ ነጻነትን በገደብ ሳይሆን፣ ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ሂደት በማካሄድ ሲቻል ነው”ብለዋል።
ዲሞክራሲ ለማምጣት ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ከአመጽ በመራቅ የዲሞክራሲ ሂደቱ እውን እንዲሆን ድጋፍ መስጠት እንደሚኖርበት ማበረታታት እፈልጋለሁ ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ ይህን የምናገረው ኢትዮጵያ በጣም ጠቃሚ አገር ስለሆነች ነው ብለዋል።
የእስረኞች መፈታት አወንታዊ እርምጃ ነው ያሉት ቲሊርሰን፣ ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት ከዚህ በበለጠ ደረጃ እንዲሰፋ ተጨባጭ እርምጃዎች መወሰድ አለባቸው ሲሉ አክለዋል።
የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ የሆነችው ኢትዮጵያ፣ በሰላም ማስከበር ስራ ላይ እያደረገችው ያለውን አስተዋጽዎ አሜሪካ እውቅና እንደምትሰጠውም ባለስልጣኑ ተናግረዋል።