በኢትዮጵያ በመገናኛ ብዙሃን ላይ የሚደረግ አፈና መቀጠሉን ከአዲስ አበባ የመጣው ዜና ያስረዳል። በዚህም መሰረት የአሜሪካን ድምጽ ሬድዮ በኢትዮጵያ ቋንቋዎች በአጭር ሞገድ እንዲሁም በሳተላይት የሚያስተላልፍው ፕሮግራም በመታወክ ላይ ይገኛል።
የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከህዝብ ዕይታ መሰወርን ተከትሎ የኤርትራ ቴሌቭዥን የሣተላይት ስርጭት መመታቱ ሲታወስ፤ በሐገሪቱ በሥርጭት ግንባር ቀደም የሆነው ፍትህ ጋዜጣ ሥለ አቶ መለስ ሁኔታ ዘገባ ይዞ በመውጣቱ በፍርድ ቤት ውሳኔ መቃጠሉ አይዘነጋም።
የኤርትራ ቴሌቭዥን አረብ ሣት ላይ የሚያስተላልፈው ፕሮግራም መታወኩን ተከተሉ አረብ ሳት የኢትዮጵያ ቴሌቭዥንም ከአረብ ሣት ላይ አውርዷል።
የአሜሪካን ድምጽ በኢትዮጵያ ቋንቋዎች የሚያስተላልፈው ፕሮግራም በተለይም የአማርኛው አገልግሎት ሰሞኑን በመመታት ላይ መሆኑን የሚገልጹት የኢትዮጵያ ምንጮች፤ ጥቃቱ በተመረጡ ፕሮግራሞች ላይ ይበልጥ ማነጣጠሩንም አክለው ገልጸዋል።