ሐምሌ ፯ ( ሰባት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- አሶሼትድ ፕሬስ እንደዘገበው ሃሙስ ጠዋት የአሜሪካና የሶማሊያ ጦር ሃይል በደቡብ ሶማሊያን በአልሸባብ ተይዞ በነበረ ቦታ ላይ በሰነዘሩት ድንገተኛ ጥቃት ብዙ የአልሸባብ ወታደሮችን ገድለዋል።
የሶማሊ ኮማንዶዎች ከአሜሪካ ወታደሮች ጋር በመሆን በሁለት ሄሊኮፕተሮች ተጉዘው ኩንያ ባሮ የሚባለውን የአልሸባብ እስር ቤት የሚገኝበትን ቦታ በመውረር በፈጸሙት ድንገተኛ ጥቃት ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ እስረኞች ተለቀዋል።
የአሜሪካ አፍሪካ እዝ ቃል አቀባይ ማርክ ቺአድል አሜሪካ የምክር ድጋፍ በመስጠት መሳተፏን ገልጸዋል። ስለጥቃቱ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ግን ተቆጥበዋል።
ከሁለት ሳምንት በፊት የአሜሪካ ጦር በአልሸባብ ወታደሮች ላይ ጥቃት ፈጽሞ ነበር። ፐሬዚዳንት ኦባማ ኢትዮጵያንና ኬንያን በመጠቀም አለሸባብን ለመውጋት ዘርግተውት የነበረውን እቅድ፣ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በመለወጥ አሜሪካ በቀጥታ በአልሸባብ ላይ እርምጃ እንድትወስድ እያደረጉ ነው። አሜሪካ በኢትዮጵያ ጦር ላይ እምነት ማጣቷ ሞቃዲሾ ካለው መንግስት ጋር በቀጥታ በመስራት በአልሸባብ ላይ የጀመረቸውን ዘመቻ አጠናክራ ቀጥላለች።