የካቲት ፳፰ ( ሃያ ስምንት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የግንባታ ተቋራጮች እንደተናገሩት ስራቸውን በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ሰርተው ለማጠናቀቅ እንዳይችሉ ችግር እየፈጠረባቸው ያለው የአማራ ዲዛይንና ቁጥጥር ስራዎች ድርጅት በመሆኑ ስራውን እንዲያቆም ጠይቀዋል፡፡
ሰሞኑን በክልሉ የግንባታ ባለሙያዎችና በጤና ጥበቃ ቢሮ መካከል በተደረገው የስድስት ወር አፈጻጸም ግምገማ ላይ የተናገሩት የተቋራጭ ድርጅት ተወካዮች፣ የአማራ ዲዛይንና ቁጥጥር ስራዎች ድርጅት ባለሙያዎች በየጊዜው በሙስና በሚጠይቋቸውከፍተኛ ገንዘብ ምክንያት መማረራቸውን ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ተቋራጮች አክለው እንደተናገሩት ከፍተኛ የሙስና ወንጀል በመስራት የሚታወቀው ይህ ድርጅት ስራውን በአግባቡ ከመስራት ይልቅ ተቋራጮችን ማስጨነቅን እንደ ዋና ስራው አድርጓል፡፡
አንድ ተቋራጭ ለተሰብሳቢው በግልጽ እንደተናገሩት በአማካሪነት የሚመደቡ የአማራ ዲዛይንና ቁጥጥር ስራዎች ድርጅት ባለሙያዎች በየጊዜው በሚጠይቋቸው ገንዘብ መማረራቸውን ገልጸው ስራውን አሰሪው ድርጅት እንዲረከባቸው ጠይቀዋል፡፡አብዛኛው በስብሰባው የተገኙ ተቋራጮች እንደተናገሩት የድርጅቱ ባለሙያዎች ከድርጅቱ ስራ ይልቅ የግል ጥቅማቸውን ሲያሳድዱ እንደሚውሉ ተናግረዋል፡፡
በስብሰባው ላይ ጥናታቸውን ያቀረቡት የጤና ጥበቃ ቢሮ መሰረተ ልማት ባለሙያ በክልሉ ከተሰሩት በርካታ ግንባታዎች መካከል ከዘጠና በመቶ በላይ በአማካሪነትና በንድፍ አውጭነት የሰራው የአማራ ዲዛይንና ቁጥጥር ስራዎች ድርጅት ነው፡፡ጥናትአቅራቢው ከሞላ ጎደል የተሰሩት ግንባታዎች በሙሉ በጥራት ችግር አደጋ ላይ መሆናቸውን በዕለቱ በቀረበው ጥናታዊ ጽሁፍ ጠቁመዋል፡፡