የአማራ ክልል የጎንደር ማረሚያ ቤት ሃላፊ የታሰሩት በፌደራል ደህንነትና አቃቢ ህግ ነው አለ

ኅዳር ፳፫ (ሃያ ሦስት)ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- ካለፈው አርብ ጀምሮ በቁጥጥር ስር የሚገኙት የጎንደር ማረሚያ ቤት ሃላፊ ኢንስፔክተር ልጃለም መሰረት ፣ ደብዳቤ እንዲያስገቡ ተነግሯቸው ለክልሉ መንግስት “ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እንዲታይ ወይም እንዲፈቱ የሚጠይቅ ደብዳቤ ቢያስገቡም፣ የአማራ ክልል መንግስት “ አንተን ያሰረህ የፌደራል ደህንነትና የፌደራል አቃቢ ህግ በመሆኑ ክልሉ አያገባውም” የሚል ምላሽ ሰጥቷል።

ኢንስፔክተር ልጃለም ለፌደራል ጠ/አቃቢ ህግ ደብዳቤ ቢያስገቡም፣ ጠቅላይ አቃቢ ህጉ አቶ ጌታቸው አምባዬ በጸና ታመው ታይላንድ በህክምና ላይ በመሆናቸው መልስ የሚሰጣቸው መታጣቱን ምንጮች ገልጸዋል። ኢንስፔክተር ልጃለም የታሰሩት ኮ/ል ደመቀ ዘውዴ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ በካቴና ታስረው እንዲቀርቡ አላደረጉም በሚል ነው።

ኢንስፔክተሩ ኮ/ል ደመቀን ከማረሚያ ቤት በማውጣት ወደ ትግራይ ክልል ወይም ወደ ማእከላዊ ለመውሰድ የተደረገውን ተደጋጋሚ ሙከራ በመቃወማቸው ሰበብ ተፈልጎ ሳይታሰሩ እንዳልቀረና እርሳቸውን በማሰር ፣ ኮ/ል ደመቀን አውጥቶ ለመውሰድ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ሊሆን እንደሚችል ምንጮች ግምታቸውን ያሰፍራሉ።

ኢንስፔክተር ልጃለም የአርማጭሆ አካባቢ ተወላጅ ናቸው። የእርሳቸውን መታሰር ተከትሎ ፖሊሶች ተቃውሟቸውን እየገለጹ መሆኑን የኢሳት የክልሉ የደህንነት ምንጮች ገልጸዋል።