(ኢሳት ዜና–ሐምሌ 12/2009)የአማራ ክልል ምክር ቤት 2ኛ አመት 7ኛ መደበኛ ስብሰባ ሰሞኑን በባህር ዳር በተካሄደበት ወቅት የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ለምክር ቤቱ አባላት እንደተናገሩት ክልሉ በቱሪዝም ዘርፍ ያገኝ የነበረው ገቢ እየተገባደደ ባለው አመት 53 በመቶ ቀንሷል።
በአማራ ክልል ያለው የቱሪዝም ገቢ በ53 በመቶ ሲቀንስ በሀገር አቀፍ ደረጃ በምን ያህል መጠን እንደቀነሰ የታወቀ ነገር የለም።
ሆኖም የመንግስት ባለስልጣናት በሃገሪቱ የቀጠለው አለመረጋጋት በቱሪዝም እንቅስቃሴው ላይ ያመጣው ተጽእኖ የለም ሲሉ መግልጫ ሲስጡ መቆየታቸው ይታወሳል።
በኢትዮጵያ ከፍተኛ የቱሪስት መዳረሻ ከሆኑት ክልሎች አንዱ በሆነው የአማራ ክልል ዘቱሪዝም ዘርፉ ላይ ከግማሽ በመቶ የበለጠ ተጽእኖ መከተሉ በሀገር አቀፍ ደረጃም ከፍተኛ ተጽእኖ ጥሎ ማለፉ የሚያጠራጥር አይሆንም።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በዚሁ በባህር ዳር በተካሄደው የአማራ ክልል ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የአማራ ክልል በሃይል አቅርቦት ችግር እየተሰቃየ ነው የሚል ቅሬታ ከተሰብሳቢዎቹ የቀረበ ሲሆን በዚህም ኢንቬስተሮችን ለመሳብ ችግር ማስከተሉ ተመልክቷል።
ኢንቨስት ለማድረግ የገቡትም በሃይል አቅርቦት ችግር ወደ ስራ መግባት አለመቻላቸውም ተገልጿል።
ባለፉት አስር አመታት በአማራ ክልል የሃይል ማከፋፈያ ባለመስራቱና በደርግ ጊዜ የተሰሩትም በማርጀታቸው የሃይል አቅርቦቱ ችግር መባባሱ ተመልክቷል።