ታኀሳስ ፲፮(አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከፌደራል ፕራይቬታይዜሽንና የመንግስት የልማት ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ተረክቦ ቦታውን ለልማት ለማዋል ዝግጅት የጀመረው የክልሉ የኮንስትራክሺንና ቤቶች ልማት ኤጀንሲ ሆቴሉን ነጻ ለማድረግ ከህዳር 15 ቀን ጀምሮ አገልግሎቱን እንዲያቋርጥ እና በውስጡ ያሉትን የግለሰብ ንብረቶች ለማስወጣት ያደረገው እንቅስቃሴ ለአንድ ወር ያህል አለመሳካቱን ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ኤጀንሲው በቁጥር ኮቤልኤ-ዋሥ/32/1108 በቀን 16/ 03/07ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ በግቢው ውስጥ የሚገኙትን የግለሰብ ንብረቶች ከ15/03/07 ዓ.ም ጀምሮ በህጋዊ መንገድ እንዲያወጡ በመጠየቅ፣ ንብረቱ ከተጠቀሰው ቀን ጀምሮ የማያወጡ ከሆነ በቤቱና በግቢው ውስጥ ለቆዩበት ጊዜ ሁሉ በቀን ሃያ ሽህ ብር እና ሌሎች ኪሳራዎችን የቤቱ ባለቤት የሆነው የክልሉ መንግስት ተወካይ የኮንስትራክሽንና ቤቶች ልማት ኤጀንሲ የሚያስከፍል መሆኑን በመግለጽ ንብረቱ እንዲነሳ በመጠየቅ ሆቴሉን አሽጎ ሰራተኞችን መበተኑ ታውቋል፡፡
ለአስራ አምስት ቀናት ቢጠብቅም ምንም ውጤት ያላየው ኤጀንሲ በ01/04/07 ዓ.ም ባወጣው ድጋሚ ደብዳቤ « መንግስት በቦታው ላይ ያቀደውን የልማት ስራ እርስዎ ንብረትዎትን ባለማውጣትዎ ምክንያት ሊያቆም ስለማይገባ በግቢው ውስጥ ያለውን ንብረት ወደ አንድ ቦታ በማሰባሰብ የልማት ስራውን ለማስቀጠል ስላስፈለገ እቃው በሚሰባሰብበት ወቅት በእርስዎ በኩል በታዛቢነት የሚኖር ሰው ሰኞ ታህሳስ 8ቀን 2007 ዓ.ም ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ሆቴሉ መግቢያ በር እንዲገኝ እያሳሰብን የእርስዎ ተወካይ ወይም ታዛቢ ባይገኝ ሌሎች ታዛቢዎች በተገኙበት በግቢው ውስጥ ያለውን ዕቃ ወደ አንድ ክፍል የሚያሰባሰብ መሆኑን እየገልጽን መንግስት ይህንን እና ሌሎች ለስራው የሚያስፈልጉ ወጭዎችን ቀደም ሲል በተሰጠዎ ማስጠንቀቂያ መሰረት ከእርስዎ እንደሚጠበቅ አንዲያውቁት እናሳስባለን፡፡” ብሎአል።
በባህርዳር ከተማ ነዋሪ የሆኑት የአቶ መለስ ዜናዊ የቅርብ ዘመድ አቶ ወልዱ ወልደ አረጋይ መንግስት ማግኘት የነበረበትን ከ900 መቶ ሺህ ብር በላይ እንዳያገኝ ያደረገ ታክሰ በማጭበርበር ወንጀል ተከሰው ወልዱና ቤተሰቡ ኃላፊነት የተወሰነ የግል ማህበር በእስራትና በገንዘብ እንዲቀጣ የምዕራብ ጎጃም ዞን የባህርዳር ምድብ ችሎት ውሳኔ ማስተላለፉን የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የውሳኔ መዛግብት ዋቢ በማድረግ መዘገባችን ይታወሳል።
የምዕራብ ጎጃም ፍርድ ቤት ባህርዳር ምድብ ችሎት ወልዱና ቤተሰቡ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር፣ አቶ ወልዱ ወልደ አረጋይ እና አቶ ብስራት ወልዱ ወልዳረጋይ የተጨማሪ እሴት ታክስ ሰብስቦ ያለማሳወቅና ያለመክፈል እንዲሁም የተጨማሪ እሴት ታክስ ባልሆነ ደረሰኝ ግብይት በማካሔድ ወንጀል በአመት ስድስት ነጥብ ሶስት ሚልዩን ብር መሰብሰባቸው መጠቀሱንና ከዚህም ለመንግስት መግባት የነበረበት ከስድስት መቶ ሺ ብር በላይ ለግል ጥቀማቸው አውለዋል በማለት ተከሳሽ ወልዱ ወልዳረጋይ በ7 አመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ አንደኛ ተከሳሽ ወልዱና ቤተሰቡ ሀላፊነቱ የግል ማህበርን በተመለከተ በህገ-ሰውነት የተሰጠው ድርጅት በመሆኑ በወንጀል ህግ አንቀፅ 90/3 መሰረት የተጨማሪ እሴት ታክስ ሰብስቦ ያለማሳወቅ፣ ያለመክፈል ወንጀልና ግብር ለመንግስት ያለመክፈል ወንጀል ክሶች እያንዳንዳቸው የብር 10 ሽህ መነሻ ቅጣት፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ ባልሆነ የደረሰኝ ግብይት ማካሔድ ወንጀል ክስ ደግሞ ብር 5 ሺህ ባጠቃላይ 25 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጫ እንዲከፍሉ ውሳኔ መተላለፉን ዘግበናል፡የባህርዳር ነዋሪዎች በድርጅቱና በልጅቻው ላይ የተሰጠውን ውሳኔ ቀልድ ነው ማለታቸውም ይታወሳል ፡፡
ከ10 ቀን በፊት ከባህር ዳር ማረሚያ ቤት ከገዢው መንግስት ባለስልጣናት በተሰጠ ቀጭን ትዕዛዝ የእስር ጊዜያቸውን ሳያጠናቅቁ ሳይሆን ሳይጀምሩ የተፈቱት አቶ ወልዱ ወልደ አረጋይ ፣ ኤጀንሲው በሰጠው ማስጠንቀቂያ መሰረት ንብረታቸውን ያላነሱ ሲሆን በኤጀንሲው ውሳኔ መሰረት ንብረታቸውን ላላነሱበትና ልማቱን ላደናቀፉበት 30 ቀናት ከ600 ሽህ ብር በላይ እንደሚጠበቅባቸው ምንጮች ገልጸዋል፡፡፡የባህርዳሩ ግዮን ሆቴልን ለረዢም አመታት በአምስት ሽህ ብር የክራይ ዋጋ ሲጠቀሙበት የነበሩት አቶ ወልዱ ወልደ አረጋይ ኤጀንሲው እንዲከፍሉ የወሰነባቸውን ገንዘብ መክፈል ሳይሆን በሌሉበት እና በህግ ጥላ ስር እያሉ በማናለብኝነት ሆቴሉ በመዘጋቱና ሰራተኞችንም በመበተኑ ላደረሰባቸው ኪሳራ የክልሉን የኮንስትራክሺንና ቤቶች ልማት ኤጀንሲን በህግ ለመጠየቅ ከጠበቆቻቸው ጋር እየተመካከሩ መሆኑን እማኞች ለዘጋቢያችን ገልጸዋል፡፡
አቶ ወልዱ ግዮን ሆቴልን የሚያክል ድርጅት የአቶ መለስ ዜናዊ ዘመድ በመሆናቸውና በትጥቅ ትግሉ ወቅት መረጃ በማቀበል ላገለገሉበት እንደውለታ ተቆርጦላቸው እጅግ እርካሽ በሆነ መንገድ በሆቴሉ ከ20 አመታት በላይ ሲጠቀሙበት መቆየታቸው በክልሉ ህዝብ ከፍተኛ ቅሬታ ያስነሳ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል። አሁንም ባለስልጣናት ደፍረው የፍርድ ቤት ትእዛዝ ለማስፈጸም እንዳልቻሉ ታውቋል።