የአማራ ክልል ምክር ቤት በጸጥታ ጉዳይ ላይ ሲመክር ዋለ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 26/2011)የአማራ ክልል ምክር ቤት  ከመደበኛ ጉባኤው በፊት  በጸጥታ ጉዳይ ላይ በማተኮር በዝግ ስብሰባ  ምክክር ሲያደርግ መዋሉ ተነገረ።

ምክር ቤቱ መደበኛ ጉባዔውን ከነገ ጀምሮ እስከ የካቲት 29 ቀን 2011 እንደሚያካሂድ የክልሉ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት አስታውቋል ።

ፋይል

በዛሬው ስብሰባ ምክር ቤቱ በሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ውይይት አድርጓል ተብሏል።

በተለይም ከትግራይ ክልል በኩል ባሉ ትንኮሳዎችና የጦርነት ስጋት በዚሁም የአማራ ክልል ሕዝብን ከጥቃት ለመከላከል በሚያስችሉ ጉዳዮች አቅጣጫ ለማስቀመት መሆኑን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

ከነገው ዕለት ጀምሮ ለሁለት ተከታታይ ቀናት ደግሞ የስድስት ወራት የአስፈፃሚ አካላት የተጠቃለለ ሪፖርት በክልሉ ርዕሰ መስተዳደር በአቶ ገዱ አንዳርጋቸው ለምክር ቤቱ ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግበት ተነግሯል።

የክልሉ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትና የክልሉን ምክር ቤት ጽህፈት ቤት እንደገና ለማሻሻል የተዘጋጁ ዓዋጆች ቀርበው በምክር ቤቱ ውይይት ይደረግባቸዋል።

የአማራ ክልል ምሁራን መማክርት ጉባዔ ቻርተር ማፅደቂያ ዓዋጅ በምክር ቤቱ ቀርቦ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ይፀድቃል ተብሎም ነው የሚጠበቀው።

ምክር ቤቱ በሚያካሂደው 12ኛ መደበኛ ጉባዔው የተለያዩ ሹመቶችን ያፀድቃል ተብሏል፡፡