(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 16/2011) የአማራ ክልል ለብአዴን ብቻ የተሰጠ ስጦታ አይደለም ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የብአዴን ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን ተናገሩ።
በባህርዳር ከ11 የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ምክክር ያካሄዱት አቶ ደመቀ ከሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ተባብረን ሀገርን ማልማት ያስፈልጋል ብለዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የብአዴን ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን የፖለቲካ ፓርቲዎችን አቅም ሳንጠቀም በትነን ቆይተናል ሲሉ ከ 11 የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ምክክር ሲያደርጉ ገልጸዋል፡፡
እናም ታሪክ መስራት እና ኃላፊነትን መወጣት አለብን ነው ያሉት፡፡
እንደ አቶ ደመቀ ገለጻ ሀገር ለአንድ ድርጅት አልተሰጠችም። ትውልዱ እና ኢኮኖሚውም ሽግግር ላይ ነው፡፡
በመሆኑም ሽግግር ላይ ለሚገኘው ትውልድ እና ኢኮኖሚ የኔ ብቻ ትክክል ነው ብሎ ማሰብ አያስፈልግም ብለዋል፡፡
አቶ ደመቀ እንዳሉት ሀገርን ለመገንባት የሁሉም ፖለቲካ ፓርቲዎች ሃሳብ ስፈልጋል፡፡
እንደ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ ገለጻ የተሻለ ፖሊሲ ያለው የፖለቲካ ፓርቲ ትልቁ ዳኛ ለሆነው ህዝብ አቅርቦ መብቱን ማስከበር ይቻላል፡፡
እናም ከድህነት ትግሉ ማፈግፈግ አሁን ላይ አያስፈልግም ነው ያሉት፡፡
አቶ ደመቀ መኮንን ገናናነታችንን እና ክብራችን እንዲመለስ የዘመኑ አርበኞች ልንሆን ይገባልም ብለዋል ፡፡
ከጥላቻ እና መጠላለፍ ልንታቀብ ይገባል ያሉት አቶ ደመቀ መኮንን በትነን የቆየነውን አቅም መጠቀም ያለብን ጊዜ አሁን ነው ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ምርጫ ሲቀርብ ውጥረቱ ይበዛል፤ ያኔ ሁሉም በየፊናው ሰዶ ማሳደድን መያያዙ ም ተገቢ አይደለም ነው ያሉት።
የህዝቡ መብት እና ጥቅም እንዲከበር ከምርጫ በፊት ጥያቄዎችን መመለሱ የሁሉም ድርሻ ሊሆን እንደሚገባም አቶ ደመቀ አሳስበዋል፡፡
ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የብአዴን ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን ጋር የተወያዩት 11ዱ የፖለቲካ ድርጅቶ ብአዴን፥ መአህድ ፥አብን ፥አገዴፓ፥ አዲሀን፥ የአማራ ሕልውና ለኢትዮጵያ አንድነትና ዲሞክራሲ፥ መኢአድ፥ ኢዴፓ፥ ኢራፓ፥ ሰማያዊ ፓርቲና አርበኞች ግንቦት ሰባት ናቸው።