የአማራ ተወላጆች ወደ መጡበት ለመመለስ ፈቃደኛ አይደሉም ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 25/2010) ከቤንሻንጉልና ኦሮሚያ ክልሎች የተፈናቀሉ ከ5 መቶ በላይ የአማራ ተወላጆች ወደ መጡበት ለመመለስ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ገለጹ።

የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ቢሮ ግን ተፈናቃዮቹ ወደ መጡበት ካልተመለሱ እነሱን ለማቋቋም የሚያስችል ምቹ ሁኔታ የለም ብለዋል።

ተፈናቃዮቹ ለመሞት ወደ ኋላ ተመለስን ወደ መጣንበት ቦታ አንሄድም በማለታቸው በኮማንድ ፖስት እየታሰሩ መሆናቸው ተሰምቷል።

የአማራ ክልል ተወላጆችን ከተለያዩ አካባቢዎች ማፈናቀል የተለመደ ክስተት ሆኖ ቆይቷል።

በተፈናቃዮቹ ላይ የሚደርሰው እንግልትና በደል ትኩረት ማጣቱ ደግሞ በዙዎችን የሚያስቆጭ ችግር ነው።

በሰሞኑ ከቤንሻንጉል ጉምዝ ካማሽ ዞን እንዲሁም ከኦሮሚያ ክልል ተፈናቅለው በባህር ዳር ከተማ የሰፈሩ ከ5 መቶ በላይ የአማራ ክልል ተወላጆች የሚረዳቸውና የሚያቋቁማቸው አተው በየቤተክርስቲያኑ እየተንገላቱ ይገኛሉ።

ከነዚሁ ተፈናቃዮች መካከልም ሕጻናትና ሴቶች እንዲሁም አረጋውያን ይገኙበታል ተብሏል።

ተፈናቃዮቹ እንደሚሉት ከቤንሻንጉልና ኦሮሚያ ክልሎች የተፈናቀሉት ተከታታይ የሆነ ጥቃት ስለሚሰነዘርባቸውና ለሕይወታቸው በእጅጉ በመስጋታቸው ነው።

ከጅማ ዞን ቡኖ በደሌና ካማሽ ዞን የተፈናቀሉት የአማራ ተወላጆች በባህርዳር ከሰፈሩ በኋላ የክልሉ መንግስት ወደ መጣችሁበት ተመለሱ ከማለት በስተቀር በዘላቂነት ለማቋቋም ፍላጎት አላሳየም።

የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤትም ያረጋገጠው ተፈናቃዮቹ የግድ ወደመጡበት ካልተመለሱ ወደ ትውልድ አካባቢያቸው መሄድ እንደሚኖርባቸው ነው።

ከተፈናቀሉ ሁለት ሳምንት እንዳለፋቸው የተናገሩት የአማራ ክልል ተወላጆች ችግራቸውን ለማስታወቅ ወደ ክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ቢሮ ቢያመሩም የሚያናግራቸው ሰው አላገኙም።

ርዕሰ መስዳድሩ በቢሮአቸው የሉም ተብሏል።

ተፈናቃዮቹ በጊዮርጊስ ቤተክርስቲያንና በተለያዩ ቦታዎች ተበታትነው እንደሚገኙ ተገልጿል።

ሌሎች ደግሞ ከባህርዳር ታፍነው ወዳልታወቀ ቦታ በኮማንድ ፖስቱ መወሰዳቸው ታውቋል።