የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት የትግራይን መንግስት ይቅርታ እንዲጠይቅ የቀረበው ጥያቄ ውድቅ ሆነ
(ኢሳት ዜና የካቲት 8 ቀን 2010ዓ/ም) በሰሞኑ ብአዴን እያደረገ ባለው ዝግ ስብሰባ ላይ የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት በሰራቸው ዜናዎችና ፕሮግራሞች የተከፉትን የህውሃት አመራሮች ለማስደሰት በማሰብ ፣ አቶ አለምነው መኮንን “ጋዜጠኞች ጥፋተኞች እንደሆኑ በማመን የትግራይን መንግስት ይቅርታ መጠየቅ አለብን” በማለት የእርሱን ደጋፊዎች በመያዝ ለሶስት ቀናት ሲከራከር ቢቆይም፣ በአቶ ገዱ አንዳርጋቸው እና በአቶ ንጉሱ ጥላሁን የሚመራው ቡድን የአለምነውን ሃሳብ በመቃወም አሸናፊ ሆኖ መውጣቱን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
“የክልሉ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት ምንም የሚነቀፍ ስራ አልሰራም” በሚል የአቶ ገዱ ቡድን ባደረገው ክርክር፣ እነ አቶ አለምነው ህወሃትን ለማስደሰት የሄዱበት መንገድ ተቀባይነት እንዳያገኝ ማድረጉን ምንጮች ገልጸዋል።
አቶ ገዱ ከስልጣን ወርደው ወደ አውስትራሊያ በአምባሳደርነት እንደሚሄዱ እየተነገረ ሲሆን፣ የክልሉን ስልጣን ዶ/ር ጥላዬ ጌቴ ሊይዙት ይችላሉ ተብሎ ይጠበቃል። አቶ ከበደ ጫኔ አቶ ገዱን ቦታ ለመያዝ ከፍተኛ ግብግብ ውስጥ መግባታቸውንም ምንጮች ገልጸዋል።
በሌላ በኩል በባህር ዳር ከተማ ትላንት ምሽት ከአንድ ሰዓት ጀምሮ በቀበሌ ሶስት እና አራት የኤሌትሪክ አገልግሎቱን በማቋረጥ ወጣቶችን የማፈስ ስራ ሲካሄድ ነበር፡፡ በአፈሳው ላለመያዝ ሲሮጡ በነበሩ ወጣቶች ላይ የአገዛዙ ወታደሮች ተኩስ የከፈቱ ሲሆን፣ የአገዛዙ አመራሮች ‘የከተማው ወጣቶች በኦሮሚያ አካባቢ የተጀመረውን ተቃውሞ ያስቀጥላሉ’ በሚል ፍራቻ በወጣቶች ላይ የ እስር ዘመቻ እያካሄዱ ነው፡፡ምሽቱን በቀበሌ አስራ አምስት አካባቢ በሚገኘው የባለስልጣኖች መኖሪያ አካባቢ ሲንቀሳቀሱ በታዩ ወጣቶች ላይም የእሩምታ ተኩስ ተከፍቶባቸዋል፡፡ አምቡላንሶች የቆሰሉ ወጣቶችን ወደ ሆስፒታል ሲወስዱ ማየታቸውን የአይን እማኞች ገልጸዋል።