የአልኮልና የጫት ተጠቃሚ ወጣቶች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ጨመረ

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 7/2010)በኢትዮጵያ የአልኮልና የጫት ተጠቃሚ ወጣቶች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩ ተገለጸ።

ፋይል

ራሳቸውን የሚያጠፉ ወጣቶችም እየተበራከቱ መምጣታቸውን አንድ ጥናት አመልክቷል።

እድሜያቸው ከ10 እስከ 24 ዓመት ከሚሆናቸው ኢትዮጵያውያን ወጣቶች መሀል 51 በመቶ የሚሆኑት የጫት ሱስ አለባቸው።

45.6 በመቶ ያህሉ ደግሞ የአልኮል መጠጥ ሱሰኛ ናቸው።

በሌላ በኩል በህገ ወጥ መንገድ ያለሀኪም ትዕዛዝ የሚሸጥ አነቃቂ መድሃኒት በወጣቱ ላይ ከፍተኛ አደጋ እያመጣ መሆኑ ተገለጸ።

ትራማዶል የተባለው መድሃኒት በአዲስ አበባ በበርካታ ተማሪዎች ዘንድ እንደሱስ እየተለመደ መምጣቱንም ለማወቅ ተችሏል።

ከሀገር ቤት የሚሰራጨው ሸገር ኤፍ ኤም እንደዘገበው ጥናቱ አስደንጋጭ መረጃዎችን ይፋ አድርጓል።

በአዲስ አበባ ሰሞኑን በወጣቶችና ስነተዋልዶ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ ላይ ጥናታቸውን ያቀረቡት የፓዝፋይንደር የወጣቶች አማካሪ የሆኑት ሲስተር ወርቅነሽ ቅሬታ ናቸው።

በውውይት መድረኩ ላይ የቀረበው ጥናትና የተላለፉት መልዕክቶች የመጪውን የኢትዮጵያ ሁኔታ ስጋት ውስጥ የሚከቱ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል።

ወጣቱ ትውልድ ሀገር ለመረከብ በሚያስችል የአእምሮ፣ የስነልቦናና የጤና ዝግጅት ላይ መድረሱ ሲበዛ አጠራጣሪ መሆኑ ተመልክቷል።

ጥናቱን ያቀረቡት ሲስተር ወርቅነሽ እንደሚሉት ራሳቸውን የሚያጠፉ ወጣቶች ቁጥር እየጨመረ ነው።

በተለይም በትምህርት ተቋማት ውስጥ የራሳቸውን ህይወት የሚያጥፉ ወጣቶች መጨመራቸውን ሲስተር ወርቅነሽ በጥናታቸው አመላክተዋል።

በሱስ የተጠመዱ ወጣቶች ቁጥር በአስደንጋጭ ሁኔታ እያሻቀበ መምጣቱም እየተነገረ ነው።

በኢትዮጵያ ወጣቶች በተለያዩ ሱሶችና ተያይዞ በሚከሰቱ የጤና ችግሮች የተነሳ ከፍተኛ አደጋ ላይ መሆናቸውን የተለያዩ ጥናቶች ያመለክታሉ።

እንደ ጥናቱ ከሆነ ጫት፣ ሺሻ፣ የአልኮል መጠጦች እና ማሪዋና የተባለውን አደንዛዥ እጽ የሚወስዱ ወጣቶች ቁጥር በአስደንጋጭ ሁኔታ እየጨመረ ነው፡፡

ሲስተር ወርቅነሽ ቅሬታ ሰሞኑን ባቀረቡት ጥናት ላይ እንደተገለጸው ከኢትዮጵያ ወጣቶች 51 በመቶ የሚሆኑት የጫት ሱስ ተጠቂ ናቸው።

45ነጥብ 6 በመቶ የሚሆኑ ደግሞ በአልኮል መጠጥ ሱስ ተለክፈዋል።

የትምባሆ ተጠቃሚዎችም ቁጥር አስፈሪ በሚባል ደረጃ መጨመሩንም ሲስተር ወርቅነሽ በጥናታቸው አመልክተዋል።

በሌላ በኩል ያለሀኪም ትዕዛዝ በህገወጥ መንገድ በሚሸጠው ትራማዶል የተሰኘ አነቃቂ እንክብል በወጣቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ መሆኑን መረጃዎች አመልክተዋል።

የህመም ማስታገሻ መድኃኒት እንደሆነ የሚገለጸው እንዲሁም የማነቃቃት ባህሪ ያለውና ሱስ የሚያስይዘው እንክብል በከፍተኛ ደረጃ ተዛምቶ በተለይ በአዲስ አበባ ቀውስ መፍጠሩን ለማወቅ ተችሏል።

የአገዛዙ ልሳን በሆነው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ የወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው አብዛኛው የአዲስ አበባ ተማሪ የትራማዶል እንክብል ሱሰኛ ሆኗል።

መድሃኒቱ ያለሀኪም ትዕዛዝ የማይሰጥ ቢሆንም መደብሮች ለተማሪዎቹ ያለትዕዛዝ እየሸጡ እንደሆነም ተመልክቷል።

ትራማዶል የሚጠቀሙ ተማሪዎች ለከፍተኛ የጤና ችግር በመዳረግ ላይ ሲሆኑ በአንድ ትምህርት ቤት 10 ተማሪዎች እንክብሉን ተጠቅመው ተዝለፍልፈው መውደቃቸውን አዲስ ዘመን ዘግቧል።

ጥናቶች እንደሚሉት ከሆነ ወጣቶች የነገ ተስፋ ሲጨልምባቸው በአደገኛ ሱስ የመጠመድ እድላቸው የሰፋ ነው።

በተለይም ተምረን ስራ ማግኘት አንችልም የሚለው የተስፋ መቁረጥ ስሜት አሁን ባለው ወጣቱ ትውልድ ዘንድ በስፋት የሚንጸባረቅ መሆኑ ተመልክቷል።