ኢሳት ዜና (መስከረም 14 ፣ 2008)
በማላዊ እስር ቤቶችን የጤናቸው ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ የሚገኙ 36 ህጻናትን ጨምሮ 387 ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ወደሃገራቸው ለመመለስ ከአሜሪካ መንግስት በኩል ድጋፍ መገኘቱን የአለም አቀፍ ስደተኞች ድርጅት (IOM) ዛሬ አርብ ገለጠ።
ኢትዮጵያዊያኑ ስደተኞች ወደ ማላዊ በህገወጥ መንገድ ገብታችኋል ተብለው የተላለፈባቸውን የዘጠኝ ወራት የእስር ቅጣት ቢያጠናቅቁም ወደኢትዮጵያ የሚመልሳቸው አካል በመጥፋቱ በእስር ቤት ለወራት መቆየታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
ከአንድ አመት በላይ በማላዊ እስር ቤቶች ሲንገላቱ የቆዩት ኢትዮጵያውያን ከቀናት በኋላ ወደሃገራቸው እንዲመለሱ ቅድመ ዝግዥት መጠናቀቁን የማላዊ ባለስልጣናት ለጋዜጠኞች ገልጸዋል።
በማላዊ የስደተኞች (IOM) ተወካይ የሆኑት ሽቴፋኒ ሮቸር በተለያዩ አካላት በተደረግ ጥረት በከፍተኛ ችግር ውስጥ የነበሩትን ኢትዮጵያውያንን ወደሃገራቸው ለመመለስ መቻሉን አስታውቀዋል።
በተጨናነቁ እስር ቤቶች ለሚገኙት ኢትዮጵያውያንን ስደተኞች የህክምና እርዳታን እያደረገ የሚገኘው ድንበር-የለሽ የሃኪሞች ቡድን (Doctors Without Borders) የተሰኘ የፈረንሳይ ግብረ-ሰናይ ድርጀት ተመላሽ ስደተኞቹ በምግብ እጥረት እና በቆዳ በሽታዎች ክፉኛ መጎዳታቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያውያኑ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላም የቅርብ የህክምና ክትትልን እንደሚፈልጉ ድርጅቱ አመልክቷል።
በማላዊ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለተመላሽ ስደተኞቹ የአልባሳት አቅርቦትን ያደረጉ ሲሆን፣ ከተመላሾቹ መካከል ስምንቱ የሳንባ በሽታ የተያዙ መሆናቸውን የፈረንሳይው ግብረሰናይ ድርጅት ገልጿል።
የማላዊ መንግስት ኢትዮጵያዉያኑ የተላለፈባቸው የእስር ቅጣት ካጠናቀቁ በኋላ በእስር ቤት ማቆየቱ ህገወጥ ተግባር ነው በማለት በርካታ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጀቶች ተቃዉሞ ሲያቀርቡ መቆየታቸው ይታወሳል።
የሃገሪቱ መንግስት በበኩሉ ስተደተኛ ኢትዮጵያዉያንን ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ በጀት በመጥፋቱ በእስር ቤት ሊያቆያቸው መወሰኑን የገለጸ ሲሆን፣ የአሜሪካ መንግስትም ድጋፍ መስጠቱ አበረታች መሆኑን አመልክቷል።