የአለማቀፍ ግጭት ተንታኝ ቡድን ባለስልጣናት አቶ መለስ ዜናዊ አርፈዋል ይላሉ::

ሐምሌ ፳፭ (ሀያ አምስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም  

ኢሳት ዜና:- የአለማቀፍ ግጭት ተንታኝ ቡድን ባለስልጣናት አቶ መለስ ዜናዊ አርፈዋል ይላሉ: ድርጅቱ በበኩሉ ዜናውን አስተባብሎአል

ኢሳት የአለማቀፍ ግጭት ተንታኝ ቡድን በእንግሊዝኛው አጣራር አይ ሲ ጂ   የውስጥ ጥናትና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡን በመጥቀስ አቶ መለስ ዜናዊ ማረፋቸውን መዘገቡ ይታወሳል።

ይህንን ተከትሎ ተቋሙ በዛሬው እለት ማስተባበያ ያወጣ ሲሆን፣ በማስተባበያውም ፣ ተቋም የአቶ መለስ ዜናዊን የጤና ሁኔታ በተመለከተ ምንም አይነት  እውቀት እንደሌለው፣ ስለወደፊቱም መናገር እንደማይችል ገልጧል።

መረጃውን በቅርብ ሲከታተሉ ከነበሩት የኢሳት ባልደረቦች መካከል አንዱ የሆነው ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና የአይሲጄ ማስተባበያ የሚጠበቅ መሆኑን፣ ነገር ግን ኢሳት በኦፊሴል ድርጅቱን አለመጥቀሱን ፣ ይልቁንም በድርጅቱ ውስጥ ከሚሰሩ ሰራተኞች መረጃው መገኘቱን ገልጧል።

ኢሳት ሌሎች ድርጅቶች መርምረው የደረሱበትን ዜና ማውጣቱን ፣ በራሱ ሰዎች መርምሮ የደረሰበት አለመሆኑን ህብረተሰቡ ግንዛቤ መያዝ እንደላበት ጋዜጠኛ ሲሳይ መክሮአል።

አቶ በረከት በቅርቡ በሰጡት መግለጫ አቶ መለስ ዜናዊ እያገገሙና በጥሩ የጤንነት ሁኔታ ላይ መሆናቸውን መጥቀሳቸው ይታወሳል።

የህወሀት ነባር ታጋይና የአቶ መለስ የፖለቲካ አባት  የሚባሉት አቶ ስብሀት ነጋ አቶ መለስ በቅርቡ ስራ ይጀምራሉ በማለት ተናግረው ነበር።

በተያያዘ ዜናም ሬዲዮ ፋና በትናንት ምሽት  የውይይት ፕሮግራሙ፦” ርዕሰ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባይኖሩ፤ አገሪቱን ማን ይመራል?” በሚል ርዕስ ሲያወያይ ማምሸቱ ተሰማ።

ከህግ አንፃር አስተያዬት እንዲሰጥበት ለአድማጮች አስተያዬት ክፍት በነበረው በዚሁ ፕሮግራም፤ከበርካታ ሰዎች  የተለያዩ ሀሳቦችና አስተያየቶች ተንፀባርቀዋል።

በውይይቱ ላይ አንድ የህግ ባለሙያው በሰጡት ቅድመ ማብራሪያ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ  በደህና ወደ ስራቸው እንዲመለሱ በመመኘት፤ ርዕሰ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባይኖር  ህጉ ግን ምንም ክፍተት እንደሌለበት እና ለምክትል ጠ/ሚኒስትሩ ሃላፊነት እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡

ውይይቱ ለአድማጮች ጥያቄ ክፍት ሲሆን፤ አንዳንድ ሰዎች  ጠንከር ያለ ተቃውሞ አዘል ጥያቄ  ሢሰነዝሩ ተሰምተዋል።

እንደነዚህ ወገኖች አባባል፤ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባይኖር፤ ምክትሉ በቋሚነት እና በጊዜያዊነት እርሳቸውን ተክቶ ሊሠራ ይችላል የሚባል ነገር የለም።ምክትሉም ሥልጣኑ ለ እኔ ይገባኛል የሚል ጥያቄ ማንሳት አይችልም። ነገር ግን ፓርላማው ሌላ ጠቅላይ ሚኒስትር የመምረጥ ስልጣን አለው።

አቶ ስብሀት ነጋ ከሳምንት በፊት ከ አሜሪካ ድምጽ ራዲዮ የ አማርኛው ክፍል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፦” ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባይኖርም በመንግስት ሥራ ምንም ክፍተት ሳይፈጠር ስርዓቱ እየቀጠለ ነው።ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህክምናውን ጨርሶ በአስር ቀናት ውስጥ ወደ ምድብ ሥራው ይመለሳል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባይመለስ ፓርላማው አብላጫ መቀመጫ ካለው ፓርቲ ሌላ ጠቅላይ ሚኒስትር ይመርጣል” ማለታቸው ይታወሳል።

በሚቀጥሉት ቀናት የሪፖርተር ጋዜጣ እንግዳ የነበሩ  ሁለት የህግ ባለሙያዎች በጉዳዩ ዙሪያ በሰጡት አስተያዬት አንድኛው በአገሪቱ ህግ መሰረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባይኖር ምክትሉ ተክቶት ሊሠራ እንደሚችል ሲያስረዱ፤ሌለኛው ግን የ አቶ ስብሀት ነጋን ሀሳብ አጠናክረዋል፦”ሌላ ይመረጣል እንጂ-ምክትሉ ተክቶት ሊሠራ አይችልም!” በማለት።

በርካታ ገለልተኛ የህግ ባለሙያዎች ፤ የአገሪቱ ህግ በዚህ ጉዳይ ክፍተት እንደሌለበት እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማይኖርበት ጊዜ ምክትሉ ተክቶት እንዲሠራ የሚፈቅድ መሆኑን  በተጨባጭ ያስረዳሉ።

ይሁንና አቶ ስብሀት ነጋ፣ራዲዮ ፋናም ሆኑ በተመሣሳይ መስመር የተሰለፉ ወገኖች  አቶ መለስ በጠና መታመማቸውን ተከትሎ ፦”ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባይኖር ምክትሉ ተክቶት እንዲሠራ የአገሪቱ ህግ ስለማይፈቅድ አዲስ የጠቅላይ ሚኒስትር ምርጫ መደረግ አለበት”የሚል አቋም በስፋት ሲያራምዱ ይደመጣሉ።

እነዚህ ወገኖች ይህን ሀሳብ ደጋግመው እያራመዱ ያሉት፤ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱ ስልጣን ከህወሀት እንዳይወጣ ለመከላከል ነው የሚል ግምት እንዳላቸው የህግ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ፤የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ድርጅት(ደኢህዴድ) ወኪል መሆናቸው ይታወቃል።

በትናንትናው  የራዲዮ ፋና ውይይት  ያስገረማቸው አንዳንድ አድማጮች ደግሞ፦”  ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጊዜያዊ እረፍት ላይ ናቸው ከተባለ፤ ሌላ ክርክር ስውጥ መግባት ለምን አስፈለገ?”ሲሉ ተደምጠዋል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide