ኢሳት (ጥቅምት 24 ፥ 2009)
በመዲናይቱ አዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ የአገልግሎት ስራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ የንግድ ድርጅቶች በኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ ምክንያት ኪሳራ እየደረሰባቸው መሆኑን አስታወቁ።
የእንግዶች መቀነስ ከተጠበቀው በላይ እየሆነ መምጣቱን የገለጹት የሆቴል ተቋማት የኢንተርኔት አገልግሎት ዕልባት ባለማግኘቱ ኪሳራን እያደረሰባቸው እንደሆነ ገልጸዋል።
ጉዳዩ የሚመለከተው የመንግስት አካል በተለይ የሆቴል ድርጅቶች እየደረሰባቸው ያለውን ኪሳራን ግምት ውስጥ በማስገባት በግብር ክፍያቸው ላይ ማስተካከያን እንዲያደርግላቸው ጥያቄን እንደሚያቀርቡም ታውቋል።
ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ ቱሪዝም ኮሚሽን የውጭ ጎብኚዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱን ያረጋገጠ ሲሆን፣ በአውሮፓ የሚገኙ በርካታ አስጎብኚ ተቋማት ወደ ኢትዮጵያ የሚደረግ የጉብኝት ዕቅድ መሰረዙን ይፋ አድርጓል።
በብሪታኒያ የሚገኙ ታዋቂ አስጎብኚ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጉዞአቸውን እንዲሰርዙ እንደዳረጋቸው ዘጋርዲያን ጋዜጣ ሰሞኑን ዘግቧል።
የቱሪስቶች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ በኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ላይ የራሱን አስተዋጽዖ እንደሚያሳድር የዘረፉ ባለሙያዎች አስረድተዋል።
በአዲስ አበባ እንዲሁም በተለያዩ ክልሎች ክፉኛ ኪሳራ ደርሶብናል ካሉት ሆቴሎች በተጨማሪ በተለያዩ የአገልግሎት መስጫ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶችም ተመሳሳይ ቅሬታን እያቀረቡ እንደሆነ ታውቋል።
በሃገሪቱ ያለው አለመረጋጋትና ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የውጭ ባለሃብቶች ላይ ጭምር ኪሳራን ማስመዝገቡ ሲገለጽ ቆይቷል።