የኔዘርላንድስ እና የአሜሪካ መንግስታት በድርቅ ለተጠቁ ኢትዮጵያውያን ዕርዳታ ለገሱ

ኢሳት (ግንቦት 9 ፥ 2008)

የኔዘርላንድ መንግስት በኢትዮጵያ በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ በምግብ እጦት ለተቸገሩ ኢትዮጵያውያን የሚሆን  የሶስት ሚሊዮን ልዩ የእርዳታ ድጋፍ ማድረጉ ተገለጸ።

የኔዘርላንድስ ውጭ ንግድ እና የእድገት ትብብር ሚኒስትር የሆኑት ሊላን ፕሉሜን ኔዘርላንድ ታይምስ ለሚባለው ድረ-ገጽ እንደተናገሩት ተጨማሪ እርዳታው ለህጻናት ምግብ አገልግሎት እንዲውል የተመደበ መሆኑን ተናግረዋል። ሚኒስትሯ የተጨማሪ 3 ሚሊዮን ዩሮ እርዳታን አስፈላጊነት ሰኞ ለመገናኛ ብዙሃን ሲናገሩ፣ “ከጥቂት ወራት በኋላ የአለም አቀፍ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ በተከሰተው የምግብ ዕጥረት በተመለከተ እርምጃ ካልወሰደ፣ በተወሰኑ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ምግብ ሙሉ በሙሉ ተማጦ ያልቃል” ብለዋል።

በመሆኑም ኔዘርላንድስ ህጻናትን ለመታደግ የ 3 ሚሊዮን ዩሮ ልዩ ድጋፍ ማድረጓን ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ከ18 ሚሊዮን በላይ የሚሆን ህዝብ የምግብ እርዳታ ፈልጊ ነው። በተለይም በምስራቅና ደቡብ ኢትዮጵያ የሚኖረው ህዝብ በድርቁ በከፍተኛ ሁኔታ የተጠቃ መሆኑን የአለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ይናገራሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካ አለም አቀፍ ተራድዖ ድርጅት ለሰብዓዊ አገልግሎት የሚውል 128 ሚሊዮን ዶላር ሊለግስ እንደሆነ ታውቋል ትናንት በአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በተሰራጨው ዘገባ ላይ ተመልክቷል። ገንዘቡም የምግብ እርዳታ፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የህጻናት አልሚ ምግብ ፣ ተንቀሳቃሽ የጤና ህክምና ፣ የዘር እህል እርዳታን ለመሳሰሉ መሰረታዊ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቶች እንደሚውል ድርጅቱ አስታውቋል።