የኔሰው ገብሬ ራሱን ባጠፋባት ዋካ ከተማ ያለው ችግር ተባብሶ ቀጥሎአል

ሚያዚያ ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- ለኢሳት የተላከው መረጃ እንደሚያመለክተው ከወረዳ ጥያቄና ከመልካም አስተዳደርና ፍትህ ጋር በተያያዘ በዳውሮ ዞን በዋካ ከተማ ከሁለት አመት በፊት የተጀመረውን እንቅስቃሴ ተከትሎ መንግስት ለዋካ እና ለተርጫ የወረዳ ከተማ ማእከልነት በመስጠት ችግሩን ለማብረድ ቢሞክርም፣  ህዝቡን ለአመጽ አነሳስተዋል የተባሉትን ግለሰቦች በማሰሩ ሌላ  ችግር እየፈጠረ መምጣቱ ታውቋል።

 

መንግስት በአቶ ዱባለ ገበየሁ፤  አባተ ኡቃ ፤  ግዛቸው ታደሰ ፤  ጎሳሁን ዶሳ፤ አብርሃም አባተ፤ ታዬ ደምሴ ፤መስፍን መሸሻ ፤ተረፈ በቀለ ፤ፍሬ ህይወት አባተ፤ ዓለሙ በቀለ ፤ማለዳ በተላ ፤ታምራት አብጤ ፤በቀለ ብላቴ ፤ዳመነ ገበየሁ፤ ተሰማ ደስታ እና ሌሎችም 23 ሰዎች ላይ ክስ መስርቷል።

ግለሰቦቹ ” መንግሥታዊ ሥር ዓቱን በኃይል ለመናድ በማሴርና በመሞከር ፣ ፀረ መንግሥት የሆነ ብሮሸር ወረቀት አዘጋጅተው ከ200 በላይ በዋካና በተርጫ ከተማ ወስጥ በመበተን፣ በተርጫ ከተማ ነዋሪ በሆኑት በወ/ሮ ጽጌረዳ በላይነህና በአቶ በሐይሉ በቡሎ መኖሪያ ቤት ውስጥ በመሰብሰብ በመንግሥት ላይ የሚዶልት ውይይት በማካሄድ ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስን ሌጋሲ በመቃወም ሌጋሲውን ‘’የሙት መንፈስ’’ በሚል በመሳደብ እንዲሁም በፌስ ቡክ የዳውሮን ዞን የፖለቲካ አመራሮች ከሚመሩት ሕዝብ ጋር በማጋጨትና የህዝቡን እምነት በመሸርሸር የአመራሩን ሕዝባዊ ተቀባይነት ማሳጣት ” በሚሉ ወንጀሎች ተከሰዋል።

በተለይ አቶ አባተ ኡቃና አቶ ዱባለ ገበየሁ ከጸረ ሕዝቦች ጋር ግንኙነት አላችሁ በሚል 141 ገጽ የያዘ ክስ በተለየ ሁኔታ ቀርቦባቸዋል። አቶ ዱባለ ገበየሁ ሰላማዊ ታጋይና የዳውሮ ዞን የደቡብ አንድነት ፓርቲ አደራጅና ኃላፊ ሲሆኑ አቶ አባተ ኡቃ ደግሞ የዩኒቨርስተ መምህር ናቸው።

ተከሳሾቹ ወደ ችሎት አንድ ጊዜ የቀረቡ ሲሆን እጅግ ብዛት ያለው ህዝብ ወደ ችሎት ለመግባት የሚያደርገው ሁኔታ ስጋት በመፍጠሩ ወደ ፍርድ ቤት እንዳይቀርቡ ተደርጓል።

ዋካ ፍትህና ነጻነት በሌለበት ሁኔታ አልኖርም በማለት ራሱን በእሳት አቃጥሎ የገደለው የመምህር የኔሰው ገብሬ ከተማ ናት።