የነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ አሳስቦናል አሉ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 30/2010) በስደት የሚገኙ የኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች ማህበር አባላት በጓደኞቻችን መፈታት ብንደሰትም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጁ ግን አሳስቦናል ሲሉ መግለጫ አወጡ።

ሕዝቡ መብቱን ለማስከበር የሚያደርገውን ትንቅንቅ በማወደስና ከጎኑ መሰለፋቸውንም በማረጋገጥ እስከ ድል ሙያዊ ትግላችን ይቀጥላል ሲሉም ቃል ገብተዋል።

“የወቅቱ የሃገራችንን ሁኔታ አስመልክቶ ከነጻ ፕሬስ አባላት የተሰጠ መግለጫ”በሚል ርዕስ በስደት የሚገኙት የነጻ ፕሬስ አባላት ባወጡት በዚህ መግለጫ በኢሕአዴግ የስልጣን ዘመን በነጻው ፕሬስ ላይ የደረሰውን በደል ዘርዝረዋል።

በጋዜጠኞቹ ላይ ከሚደርሰው እስር፣እንግልትና ወከባ ባሻገር በጋዜጠኞቹ ንብረት ላይ ጭምር ዘረፋ መካሄዱንም አስታውሰዋል።

ነጻውን ፕሬስ ካዳፈነ በኋላ ሃገሪቱን ያለከልካይና ያለጠያቂ የሚዘርፉበት ሁኔታን በማመቻቸት ይህንን ሲከውኑ መቆየታቸውን ዘርዝረዋል።

“ምዝበራው፣ግፍና አፈናው ከመጠን በማለፉ በተለይ ካለፉት 2 አመታት ወዲህ የሕዝቡ ቁጣ ዳር እስከዳር ገልፍሎ ጥያቄውን ወደ ስርአት ለውጥ ከፍ አድርጎታል።”ይላል መግለጫው።

በሃገሪቱ ውስጥ የተፈጠረውን ውጥረት ተከትሎ የሙያ አጋሮቻችን መፈታት ቢያስደስተንም እንደገና በሃገሪቱ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ መታወጁ አሳስቦናል በማለት አዋጁ እንዲነሳም ማህበሩ በመግለጫው ጥሪውን አቅርቧል።

የሕዝብን ጥያቄ በአግባቡ ከመመለስ ውጭ አፈና መፍትሄ አያመጣም የሚለው የኢነጋማ መግለጫ በአዋጁ ሳቢያ ለሚከተለው ደም መፋሰስ ተዋናይና ተባባሪ የሆኑ ወገኖች ሁሉ በሕግ የሚጠየቁበት ግዜ እንደሚመጣም አመልክቷል።

በአጠቃላይ በሃገራችን የተፈጠረውን ቀውስ ለመሻገር የሕዝብ ጥያቄ ከመመለስ ውጪ መፍትሄ አይኖርም ያለው የኢነጋማ መግለጫ ሳይረፍድ ስልጣን ላይ ያለው ቡድን ይህንን ሃላፊነቱን እንዲወጣም አሳስቧል።