ኢሳት (የካቲት 21 ፥ 2008)
በአለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ዋጋ የቀነሰ ቢሆንም መንግስት ተገቢውን ቅናሽ አላደረገም በሚል የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ቅሬታን አቀረቡ።
ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት በበኩላቸው በአለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ዋጋ ካልፈው አመት ጀምሮ የ40 በመቶ ቅናሽን ቢያሳይም መንግስት ተግባራዊ ያደረገው ቅናሽ ከ12 በመቶ እንደማይበልጥ መግለጻቸውን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ታደሰ ሃይለማሪያም፣ መንግስት የሚገዛው ነዳጅ የወደብ ክፍያ የትራንስፖርት እና ሌሎች ወጪዎች የሚካተቱበት በመሆኑ ዋጋው አሁን ካለበት ሊቀንስ እንደማይችል ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
ይሁንና፣ ቅሬታን እያቀረቡ ያሉ የተለያዩ አካላት በሃገር ውስጥ ለሽያጭ እየቀረበ ያለው የነዳጅ ዋጋ መጠን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚታየው የነዳጅ ቅናሽ ጋር የተመጣጠነ እንዳልሆነ አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ አብዛኛው የነዳጅ ፍጆታዋን ከጎረቤት ሱዳን የምታስገባ ሲሆን በየአመቱም ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪን እንደምታደርግ ይነገራል።
ሀገሪቱ በየአመቱ ለነዳጅ ፍጆታ የምታወጣው ገንዘብ ለወደብ አገልግሎት ከምትከፍለው ክፍያ ጋር የተቀራረበ መሆኑንም ከመረጃዎች ለመረዳት ተችሏል።