(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 11/2010) የነዳጅ አቅርቦትን የማስተጓጎል ዘመቻ ለአንድ ሳምንት መራዘሙ ተገለጸ።
በኦሮሚያና አማራ ክልሎች ላይ ውጤታማ የተባለውን ዘመቻ በሌሎች አካባቢዎችም ለማስፋፋት በሚል የተራዘመው ዘመቻ ሌሎች እንቅስቃሴዎችም በተጓዳኝ እንደሚኖሩት ታውቋል።
በአንድ ሳምንቱ ዘመቻ በአገዛዙ ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠር የተቻለ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ነዳጅ ወደ ሀገር ቤት እንዳይገባ፣ በሀገር ውስጥም የነዳጅ ማመላለሺያ ተሽከርካሪዎች እንዳይንቀሳቀሱ የሚያደርገውን ዘመቻ የደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች፣ ጋምቤላ ቤንሻንጉልና ሌሎች ክልሎች እንዲቀላቀሉ ጥሪ ተደርጓል።
በአማራና በኦሮሞ ወጣቶች በጋራ እየተካሄደ ያለው የነዳጅ ስርጭትን የማስተጓጎል ዘመቻ እንዲቀጥል የተፈለገው በሁለት ምክንያቶች መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
አንደኛው ዘመቻው በሌሎቹም የኢትዮጵያ አካባቢዎች እንዲካሄድ በመፈለጉ ሲሆን ሌላው ደግሞ የመከላከያ ሰራዊት ለቆ እስኪወጣ ዘመቻው መቀጠሉ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ መሆኑ ተገልጿል።
የመጀመሪያው ዙር ዘመቻ ትላንት መጠናቀቁን ተከትሎ ከቄሮዎች የተላለፈው መልዕክት ላይ እንደተገለጸው ዘመቻው ካለፈው ሳምንት ዘመቻ የተገኘውን ልምድ መነሻ በማድረግ ከኦሮሚያና ከአማራ ክልሎች በተጨማሪ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች እንዲስፋፋ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
በመሆኑም ዘመቻው ካለፈው ሳምንት በበለጠ ተጠናክሮ እንዲካሄድ የኢትዮጵያ ወጣቶች በያሉበት የነጻነት ትግሉን እንዲቀላቀሉ ጥሪ ተደርጓል።
ከዛሬ ጀምሮ እስከመጪው ሰኞ የቀጠለው የነዳጅ ስርጭት ላይ የሚደረገው የማስተጓጎል ዘመቻ በዋናነት ለነዳጅ አመላላሽ ቦቴ ባለቤቶችና ተሽከርካሪዎች የተላለፈ ነው።
ወደ ሀገር ቤት ነዳጅ ይዘው እንዳይጓጓዙና የገቡም ካሉ ከአንድ አካባቢ ወደሌላ እንዳይንቀሳቀሱ የሚያደረግ ነው።
ይህን የህዝብ ጥሪ ተላልፎ በሚገኝ የነዳጅ አመላላሽ ተሽከርካሪ ላይ ርምጃ የሚወሰድ መሆኑን አስተባባሪዎቹ አስጠንቅቀዋል።
በዚህኛው ዙር ዘመቻ ከነዳጅ ዝውውር ማስተጓጎል በተጨማሪ ሌሎች ተግባራትም ሊፈጸሙ እንደሚችሉ ተገልጿል።
የመብራትና የውሃ ስርጭትን የማስተጓጎል ርምጃ ተፈጻሚ ሊሆን እንደሚችል ቢገለጽም መቼ እንደሚከናወን አልተጠቀሰም።
የኢትዮቴሌኮም ቀጣዩ የእቀባ ዘመቻ የሚደረግበት ተቋም ሊሆን እንደሚችል የኢሳት የመረጃ ምንጮች ገልጸዋል።
የኢትዮ ቴሌኮም በአገዛዙ ቁጥጥር ስር የሚገኝ ለደህንነትና ስለላ ተግባር ትልቅ ድርሻ ያለው ሲሆን በዚህ ተቋም ላይ የሚደረግ የእቀባ ዘመቻ አገዛዙን ክፉኛ ሊጎዳው እንደሚችል ተጠቁሟል።
በቀን ከ40ሚሊየን ብር በላይ ገቢ የሚሰበስበው የኢትዮ ቴሌኮም የአንድ ቀን አድማ ቢመታበት ከፍተኛ ኪሳራ ሊገጥመው እንደሚችል ይነገራል።
ለአንድ ሳምንት የተካሄደው ዘመቻ ምንም ጉዳት አላመጣም የሚል መግለጫ በአገዛዙ ባለስልጣናት በኩል እየተሰጠ ነው።
በማህበራዊ ድረ ገጾች የተናፈሰ ወሬ እንጂ ከዚያ ያለፈ ጉዳት አላመጣም ሲሉ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሰሞኑን መግለጻቸው ይታወሳል።
ኢሳት በሰበሰባቸው መረጃዎች ላይ እንደተመለከተው የነዳጅ ማስተጓጎሉ ዘመቻ በሀገሪቱ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል።
የአማራ ክልል ባለስልጣናት በዘመቻው ምክንያት ስራ ያቆሙ ፋብሪካዎችና ድርጅቶችን በተመለከተ እየመከረበት እንደሆነ ለኢሳት የደረሰው መረጃ አመልክቷል።
የአዲስ ፎርቹን ጋዜጣ መዲናዋ የገጠማትን ቀውስ ሲገልጸው ‘’አዲስ አበባን ነዳጅ ጠማት’’ በማለት ነው።
ሪፖርተር ጋዜጣ በበኩሉ የነዳጅ ማመላሽያ ቦቴዎች በኮማንድ ፖስቱ ወታደሮች ታጅበው ወደ አዲስ አበባ መግባታቸውን ባለፈው ሳምንት ዘግቧል።
በሰሜን ኢትዮጵያ በአንድ ሳምንት ውስጥ ሶስት የነዳጅ ማመላለሽያ ቦቴ ተሽከርካሪዎች የህዝብን ጥሪ ተላልፈው በመገኘታቸው ከጫኑት ነዳጅ ጋር እንዲቃጠሉ መደረጋቸውን መዘገባችን የሚታወስ ነው።