(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 4/2010) በቄሮዎች የተጠራው የነዳጅ አቅርቦትን የማስተጓጎል ዘመቻ ዛሬ ተጀመረ።
ለአንድ ሳምንት የተጠራው ይህ ዘመቻ ነዳጅ የጫኑ ቦቴ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ፣ በሀገር ውስጥም ከአንድ አካባቢ ወደሌላ እንዳያመላልሱ የሚያደርግ ነው።
ዛሬ ዘመቻው ሲጀምር አዲስ አበባ ተጽዕኖው ጎልቶ ከታየባቸው አካባቢዎች የሚጠቀስ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።
በርካታ ማደያዎች ነዳጅ የላቸውም። በየቦታው ነዳጅ አመላላሽ ቦቴዎች ቆመው እንደሚታዩ የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ከሱዳን የሚገባው የነዳጅ መስመርም እንዲሁ የዘመቻው አካል መሆኑ ታውቋል።
ከመጋቢት 4 እስከ መጋቢት 11 2010 የተጠራው የነዳጅ አቅርቦትን የማስተጓጎል ዘመቻ በተለይም በኦሮሚያ ክልል ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ መደረጉን መረጃዎች ያመለክታሉ።
በኦሮሞ ወጣቶች ወይም ቄሮዎች የተጠራው ዘመቻ የሞያሌው ጭፍጨፋ ተከትሎ ቁጣን ለመግለጽ የታሰበ መሆኑም ታውቋል።
ከዚህም ባለፈ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳና የመከላከያ ሰራዊት ከክልሉ እንዲወጣ ለማስገደድ በሚል የተጀመረው ዘመቻ በመጀመሪያው ቀኑ የነዳጅ ስርጭቱ ላይ ከፍተኛ ማስተጓጎል ማሳደሩን ለማወቅ ተችሏል።
በጅቡቲ መስመር ነዳጅ በማመላለስ ስራ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች በርካቶቹ ከትላንት ምሽት አንስቶ ተሽከርካሪዎቻቸው እንዳይንቀሳቀሱ ማድረጋቸው ተገልጿል።
ባለፉት ሶስት ዓመታት በነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ በጅቡቲ መስመር የሚሰሩ የነዳጅ አመላላሽ ተሽከርካሪ ባለንብረቶች ጥቃት ሲደርስባቸው የስራ ማቆም አድማ ለማድረግ ወስነው እንደነበርም የሚታወስ ነው።
የቄሮዎቹን ዘመቻ ተከትሎም ባለንብረቶቹ ከእንቅስቃሴ ውጭ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል።
በተለያዩ አካባቢዎች የቦቴ ነዳጅ ተሽከርካሪዎች በብዛት ቆመው የሚታዩ ሲሆን ማደያዎች ቤንዚን የለም የሚል ማስታወቂያ በመለጠፍ ደምበኞቻቸውን ሲመልሱ መዋላቸውን በፎቶግራፍና በቪዲዮ ተደግፈው የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።
በአዲስ አበባ ከዋዜማው ጀምሮ ዘመቻው የፈጠረው ውጥረት ተስተውሏል።
በአብዛኞቹ የከተማው የነዳጅ ማደያዎች ረጃጅም ሰልፎች የሚታዩ ሲሆን እስከዛሬ ጠዋት ድረስ ወረፋ በመጠበቅ እዚያው ያደሩ እንዳሉም የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
ከአዲስ አበባ ወደ ወልቂጤ ሲጓዝ የነበረ አንድ ኢሳት ያነጋገረው መንገደኛ በርካታ የነዳጅ ማመላለሺያ ቦቴ ተሽከርካሪዎች በመንገድ ላይ ቆመው ማየቱን ተናግሯል።
ገና ከመጀመሪያው ቀን አገዛዙን ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ የከተተው የነዳጅ አቅርቦትን የማስተጓጎል ዘመቻ በሰሜን ኢትዮጵያ ቀድሞ የተጀመረውን ማስተጓጎል እንዳጠናከረው ይነገራል።
ባለፉት ሁለት ወራት ከአምስት በላይ የነዳጅ አመላላሽ ተሽክርካሪዎች በታጣቂዎች የጋዩ ሲሆን ከፍተኛ ኪሳራ በማስከተሉ ከመተማ ጎንደር ያለው መስመር በውጥረት ላይ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
በቄሮዎች የተጠራውን ዘመቻ ተከትሎም ከመተማ፣ ጎንደርና ከመተማ ሁመራ ነዳጅ የሚያመላልሱ ተሽከርካሪዎች ሳይንቀሳቀሱ መዋላቸውን ለማወቅ ተችሏል።
ለአንድ ሳምንት የሚቆየው ዘመቻ የሚያስከትለውን ጉዳት የተገነዘበው አገዛዙ በኮማንድ ፖስቱ አማካኝነት ማስፈራራት መጀመሩም ታውቋል።
የነዳጅ ቦቴ ተሽከርካሪ ባለንብረቶችን ጥበቃ ሊደረግላችሁ ስለሚችል ወደ ስራ ተመለሱ በሚል እያስፈራራ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
በሌላ በኩል በአገዛዙ የደህንነት መስሪያ ቤት የተቀናበሩ የጥፋት ርምጃዎች በቄሮዎች ስም ሊፈጸሙ እንደሚችሉ የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
በተለይም በአዲስ አበባና በአንዳንድ ከተሞች በነዳጅ ማደያ ስፍራዎችና ህዝብ በሚሰበስብባቸው አካባቢዎች በደህንነት መስሪያ ቤቱ አደጋ በመጣል ዕልቂት ለመፈጸም በመታቀዱ ህዝቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ የአገዛዙን ሴራ እንዲያከሽፈው ጥሪ ተደርጓል።