(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 7/2010) ለአንድ ሳምንት የተጠራው የነዳጅ ስርጭትን የማስተጓጎል ዘመቻ ለአራተኛ ቀን መቀጠሉ ታወቀ።
በሰሜን ጎንደር ከመተማ የተነሳ አንድ የነዳጅ ቦቴ ተሽከርካሪ ጭልጋ ላይ ጥቃት እንደተሰነዘረበት የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በኦሮሚያ ክልል የነዳጅ አቅርቦትን ለማስተጓጎል እየተካሄደ ያለው ዘመቻም መጠናከሩን መረጃዎች ያሳያሉ።
በሌላ በኩል የጭሮ ከተማ ከንቲባ ዛሬ በኮማንድ ፖስቱ መታሰራቸውን ለማወቅ ተችሏል።
በነዳጅ ዝውውር ላይ የተጠራው የማስተጓጎል ዘመቻ በአራተኛ ቀኑም የነዳጅ ስርጭቱ ላይ ከፍተኛ መስተጓጎል መፍጠሩን መረጃዎች ያመለክታሉ።
የነዳጅ አመላላሽ ቦቴ ተሽከርካሪዎች የተጠራውን ዘመቻ ተከትሎ በየደረሱበት አካባቢ ቆመው የሚታዩ ሲሆን በወታደራዊ አጀብ የሚንቀሳቀሱ የተወሰኑ ተሽከርካሪዎች እንዳሉም የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
ዛሬ በቡራዩ ሰባት የነዳጅ አመላላሽ ቦቴ ተሽከርካሪዎች መንቀሳቀስ ሳይችሉ ለመቆም መገደዳቸው ታውቋል።
በአዲስ አበባ መውጪያ አካባቢዎች እንዲሁ በርካታ የነዳጅ ቦቴዎች ቆመው የሚታዩ ሲሆን ከመነሻው ጅቡቲም መንቀሳቀስ ያልቻሉት ለአራተኛ ቀን ባሉበት መቆማቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ዘመቻው በተለያዩ አካባቢዎች የፈጠረው ተጽእኖ የቀጠለ ሲሆን በተለይ በአዲስ አበባ ማደያዎች ማስታወቂያ በመለጠፍ አገልግሎት እንደማይሰጡ ገልጸው ደምበኞቻቸውን እየመለሱ ናቸው።
አገዛዙ የተፈጠረ ችግር የለም የሚል መግለጫ እየሰጠ ባለበት በዚህን ወቅት ከተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች የሚደረሱን መረጃዎች የነዳጅ እጥረቱ እየተባባሰ መምጣቱን የሚያመላክቱ ናቸው።
ይህ በእንዲህ እንዳለም ትላንት ነዳጅ ጭኖ ከመተማ የተነሳ ቦቴ ተሽከርካሪ ጭልጋ ሲደርስ ጥቃት እንደተፈጸመበት የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
የተጠራውን ዘመቻ ወደጎን በመግፋት በጉዞ ላይ የነበረው ነዳጅ አመላላሽ ተሽከርካሪ ርምጃ የተወሰደበት ሲሆን ከነጫነው ነዳጅ መቃጠሉን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
ከትላንት በስቲያም በጎጃም አማኑዔል በተባለ አካባቢ የተጠራውን ዘመቻ ባለመቀበል ሲንቀሳቀስ በነበረ የነዳጅ አመላላሽ ተሽከርካሪ ላይ ርምጃ መወሰዱ የሚታወስ ነው።
በሌላ በኩል በኦሮሚያ ባልስልጣናት በኮማንድ ፖስቱ መታሰራቸው መቀጠሉ ታውቋል።
ዛሬ በቀድሞ አጠራሯ አሰበ ተፈሪ የአሁኗ ጭሮ ከተማ ከንቲባ አቶ ጣሃ ዋቆ ታስረው ወዳልታወቀ ስፍራ መወሰዳቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል ባልስልጣናት ላይ የሚወሰደው የእስር እርምጃ ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን በትላንትናው ዕለት የክልሉ የፍትህ ቢሮ ቃ አቀባይ አቶ ታዬ ደንዳአ መታሰራቸው ተገልጿል።
በእስከ አሁንም አምስት የክልሉ ሃላፊዎች በኮማድ ፖስቱ መታሰራቸው ታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ቄሮ የአንድ ሳምንቱን የነዳጅ ማስተጓጎል ዘመቻን ለማራዘምና በሌሎች እንቅስቃሴዎች የተጠናከረ የአድማ ዘመቻ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
የህዝባዊ እምቢተኝነት የተለያዩ ተግባራትን መነሻ በማድረግ በኢትዮጵያ ያለውን አገዛዝ የሚያላሽቁና በአስገዳጅ ሁኔታ ከስልጣን እንዲወገድ የሚያደርጉ ስልቶች እየተመከረበት መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል።