የትግራይ ክልል አስተዳደር ያፈናቀላቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ቆቦ ሰፍረዋል

የትግራይ ክልል አስተዳደር ያፈናቀላቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ቆቦ ሰፍረዋል
( ኢሳት ዜና ነሐሴ 29 ቀን 2010 ዓ/ም ) የራያ ተወላጆች ህወሃት በሚያዛቸው ወታደሮች አካባቢያቸውን ለቀው እንዲወጡ መደረጋቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገረዋል። በርካታ ወጣቶች የራያን የማንነት ጥያቄ በማንሳታቸው በርካታ ወታደሮችን ያስገቡት የህወሃት መሪዎች፣ በወጣቶች ላይ ጥቃት እየፈጸሙ ነው። ከ400 በላይ ተፈናቃይ ወጣቶች ከአላማጣ ተፈናቅለው ወደ አማራ ክልል በመሄድ ቆቦ ከተማ ላይ የሰፈሩ ሲሆን፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ደግሞ ማደኛ ወጥቶባቸው እየተፈለጉ ነው።
ብዙዎቹ ተፈናቃዮች፣ መምህራን፣ የግብርና ሰራተኞች፣ አርሶአደሮችና የተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤት ሰራተኞች ናቸው። ከተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች የመጡ ዜጎችን በራያ አካባቢ ለማስፈር እንቅስቃሴ መጀመሩን ተከትሎ፣ የአካባቢው ተወላጆች መሬት ሳያገኙ እንዴት ከሌላ አካባቢ የመጡ ሰዎች መሬት ያገኛሉ የሚል ጥያቄ ያቀረቡ ሰዎች መፈናቀላቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የብአዴን ማእከላዊ ኮሚቴ በቅርቡ ክልሎች እንደገና እንዲዋቀሩና የማንነት ጥያቄዎችም እንዲመለሱ እንደሚታገል ያስተላለፈው ውሳኔ፣ ህወሃት በራያ አካባቢ ያለውን የሰው ሃይል ቁጥር መጠን ለመቀየር ከተለያዩ አካባቢዎች ሰዎችን የማስፈር እቅድ እንዳለው የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ። የህወሃት ድርጊት በአካባቢው ደም መፋሰስ እንዳያስከትል ስጋት አለ። የፌደራል መንግስት ጣልቃ እንዲገባም የአካባቢው ነዋሪዎች ጥያቄዎችን እያቀረቡ ነው።