የትግራይ ክልል ምሁር የዶክተር አብይ አህመድን ጠቅላይ ሚኒስትርነት ተቃወሙ።

የትግራይ ክልል ምሁር የዶክተር አብይ አህመድን ጠቅላይ ሚኒስትርነት ተቃወሙ።
(ኢሳት ዜና መጋቢት 25 ቀን 2010 ዓ/ም) ጉዳዩን አስመልክቶ ለአሜሪካ ድምጽ የአማርኛው ፕሮግራም ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ቃለ ምልልስ የሰጡት የትግራይ ተወላጅ የሆኑ ምሁር ፣ዶክተር አብይ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናሉ ብለው ፈጽሞ እንዳልጠበቁ በመጥቀስ በምርጫው ቅሬታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል። በህዝባዊ አመጹ ወቅት በትግራይ ተወላጆች ላይ ጥቃት ሲደርስ አላወገዙም በማለት ዶክተር አብይን የከሠሱት እኚሁ ምሁር፣ ከዶክተር አብይ ይልቅ የደኢህ ዴዱ ሽፈራው ሽጉጤ ለቦታው ብቁ እንደሆኑ እና እርሳቸውን ጠብቀው እንደነበር ገልጸዋል።
“ሽፈራው ሽጉጤን የመረጡበት ምክንያት ምን እንደሆነ” ከጋዜጠኛው ለቀረበላቸው ጥያቄ ሢመልሱም፦”አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በትግራይ ተወላጆች ላይ ጥቃት ሲደርስ አውግዘዋል” ሲሉ መልሰዋል። ምሁሩ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርነትን ሹመት ውሳኔ፣ በራሳቸው አካባቢና በአንድ ያልተረጋገጠ ክስተት ቅርጫት ውስጥ ሊከቱት መሞከራቸው አስተያዬቱን ያደመጡትን ሁሉ አስገርሟል። ዶክተር አብይ፣ ለግንባሩ ሊቀመንበርነት ይወዳደሩ ዘንድ አቶ ለማ መገርሳ ጋር የድርጅት ቦታቸውን ከተቀያየሩ ጀምሮ በከፍተኛ የህወኃት ካድሬዎች፣ በፌስቡክ ተከፋይ ሰሀፊዎች ፣ እንደ አይጋ ፎረምና ትግራይ ኦን ላይን በመሣሰሉ ድረ ገጾች ከፍ ያለ የስም ማጥፋት ዘመቻና የተቃውሞ ቅስቀሳ ሲደረግባቸው መቆየቱ ይታወሳል።
ተቃውሞውና ትችቱ አሁንም ከተመረጡ በኋላ ጨርሶ ሊቆም አለመቻሉ ፣ የአዲሱን ጠቅላይ ሚብኒስትር መጪ ጊዜያት ከባድ እንደሚያደርገው ብዙዎች ይናገራሉ። አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በህወኃት ካድሬዎች ጫጫታ በመደናገጥና ከአቋማቸው በማፈግፈግ አቶ ኃይለማርያም የሠሩትን ስህተት እንዳይደግሙ ያስጠነቀቁት እነኚሁ ወገኖች፣ ተሿሚው የኢህአዴግ ተመራጭ ቢሆኑም እዚህ ሥፍራ የደረሱት በሕዝብ መስዋዕትነት እንጂ በግንባሩ ችሮታ አለመሆኑን በማጤን በእያንዳንዷ ንግግራቸውና እርምጃቸው ከህዝብ ጋር መሆናቸውን እያረጋገጡ እንዲጓዙ መክረዋል።
አቶ ለማ መገርሳ ሰሞኑን ከኦቢኤን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ዶክተር አብይ እዚህ ቦታ የደረሱት በእልህ አስጨራሽ ትግል እንደሆነ በመጥቀስ፣ከእስካሁኑ ይልቅ ከፊታችን ያለው ጉዞ ከባድ መስዋዕትነት የሚጠይቀን ነው ማለታቸው አይዘነጋም። በመኾኑም ከወዲሁ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ የትግራይ ህዝብ ጠላት ናቸው፣ ከእርሳቸው ይልቅ ሽፈራው ሽጉጤ ነበሩ መሆን ያለባቸው” ከሚሉና ሁሌ ታዛዥና ሎሌ እንጂ በራሱ የቆመ ሰው ከማይፈልጉ ካድሬዎች በሚነገሩ ማስደንገጫ ቅስቀሳዎች ቦታቸውን እንዳይለቁ ሲሉ አክቲቪስቶች አዲሱን ተሿሚ ያሣስባሉ።
የክልሉ ልሳት የሆነው ድምጸ ወያነ ራዲዮ በበኩሉ ዶክተር አብይ የኢህ አዴግ ሊቀመንበር ሆነው መመረጣቸውን ተከትሎ አሰባሰብኩት ባለው መጠይቅ 64 በመቶው የትግራይ ሕዝብ በዶክተር አብይ መመረጥ ደስተኛ እንደሆነ እና 36 በመቶ ያህሉ የትግራይ ህዝብ ደስተኛ እንዳልሆነ ይፋማድረጉ ይታወቃል።የትግራይ ሕዝብ አቶ መለስን መቶ በመቶ እንደሚደግፍ ሲያስተጋባ የቆዬው ድምጸ ወያነ፣ ዶክተር አብይን 36 በመቶው እንደሚቃወማቸው መዘገቡ የክልሉ ፖለቲካዊ አሰላለፍ እየተቀዬረ ለመምጣቱ አመላካች እንደሆነ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ አስተያዬታቸውን ይሰጣሉ።