ጥቅምት ፲፫ (አስራ ሶስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-“አቦይ ስብሃት ፤’ሥልጣን ከአማራውና ከኦርቶዶክሱ በመራቁ ደስ ብሎናል’ሲሉ መናገራቸው አገር ወዳዶቹን የትግራይ ልጆች አሳዝኖናል ሲሉ በሲያትልና አካባቢው የሚኖሩ ተወላጆች ገለጹ።
የትግራይ ተወላጆቹ የ አቶ ስብሀት ነጋን ወደ በርሊን መምጣት በማስመልከት ባወጡት መግለጫ፤ አቶ ስብሀት ገዛ ተጋሩ በተባለው ፓልቶክ ክፍል ቀርበው ሥልጣን- ከአማራውና ከ ኦርቶዶክሱ በመራቁ ደስ ብሎናል በማለት በመናገራቸው ምስጢሩ ያልገባቸው አንዳንድ የዋሀንን ቢደሰቱም፤ እኛ አገር ወዳድ የትግራይ ተወላጆች ግን በጣም አዝነናል”ብለዋል።
<<ሕወሃት ከተመሠረተ ጀምሮ የትግራይን ሕዝብ- ከእግዚአብሔርና ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ሲያጋጨው ስለመቆየቱ እኛ አገር ወዳድ የትግራይ ተወላጆች በየአጋጣሚው ስናስጠነቅቅ መቆየታችን ይታወሳል:>>ያሉት የትግራይ ተወላጆቹ፤ “ አሁንም በህይወት የቀሩት የሕወሃት መሪዎች ካለፈው ጥፋታቸው ተምረው፤ ወደ ሕዝባቸውና ወደ አገራቸው እንዲመለሱ አጥብቀን እናሣስባለን>>ብለዋል።:
የትግራይ ተወላጆቹ ሲቀጥሉም፦”ዛሬም የሕወሃት አባላትና ደጋፊዎች ልብ እንዲገዙ እንመክራለን::ምክንያቱም ሕወሃቶች በእድሜአቸው ትልቅ ቢሆኑም፤ ካለፈው ጥፋታቸው ሊማሩ አልቻሉም::ይህን ጽሁፍ እንድናውጣ ያስገደደንም ባለፈው አቶ ስብሃት ነጋ የተናገሩት ነገር ነው”ብለዋል።
አዛውንቱ አቶ ስብሀት፤ ሥልጣን ከአማራና ከኦርቶዶክስ ስለመራቁ አስመልክተው የተናገሩትን ያወሱት የትግራይ ተወላጆቹ፤<<አሁንም ይህን የከፋፍለህ ዘዴአቸውን በሥራ ላይ ለማዋል ወደ አውሮፓ ሊመጡ መሆናቸውን ስምተናል:: በመሆኑም የሕወሃት ደጋፊ የሆናችሁ ወገኖች የአቶ ስብሃት ነጋን የረቀቀ የከፋፍለህ ግዛ ሴረኝነት በመረዳት ፤መርዝ ንግግራቸውን ለመስማት እንዳትሄዱ እናሳስባለን>> ሲሉ ጥሪ አድርገዋል።
<<ሕወሃትና አቦይ ስብሃት እንኳን ለሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቅርና፤ ቁምንለታል ለሚሉት ለትግራይ ሕዝብ አይጨነቁም ሲሉም>> እነኚሁ በሲያትል የሚኖሩት የትግራይ ተወላጆች ገልፀዋል።
እንደ እነሱ አባባል ፤ዛሬ ትግራይ 57 ወረዳዎች ያሏት ሲሆን፤ 38ቱን ወረዳዎች የሚያስተዳድሩት የአድዋ አውራጃ ተወላጆች ናቸው::
እንዲሁም በትግራይ ያሉት የአራቱም ዞኖች አስተዳዳሪዎች በሙሉ የአድዋ ተወላጆች መሆናቸውን ያመለከቱት የትግራይ ተወላጆቹ፤<<ታዲያ ህወሀቶች ለ17 ዓመታት አብረዋቸው ለታገሉ የትግራይ ልጆች ያልሆኑ፤ እንዴት ለሌላው ኢትዮጵያዊ ሊቆረቆሩ ይችላሉ?>> ሲሉ ጠይቀዋል።
አቶ ስብሀት ሰሞኑን ከጀርመን የምክር ቤት አባላት ጋር በበርሊን በተደረገ ስብሰባ ላይ፦<<የኢትዮጵያ ህዝብ ለዲሞክራሲ ብቁ አይደለም> ማለታቸውን፤ የደቸ ቨለ ዘገባ ያመለክታል።
በማያያዝም፦<<የሕወሃት መሪዎች በሚፈጽሙት ሴራ የትግራይ ሕዝብ ያለፈለት የሚመስላችሁ ወገኖች ብዙ ናችሁ>> ያሉት የትግራይ ተወላጆቹ፤ ሀቁ ግን እየተባለ ካለው ነገር የሚለይ መሆኑን አስረድተዋል።
አክለውም፦<<የሕወሃት መሪዎች ነክተውና ነካክተው ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንን በቁጣና በስሜት እንድትናገሩና እንድትጽፉ ያደርጋሉ::ከዚያም ያንን በቁጣ የፃፋችሁትንና የተናገራችሁትን እየጠቀሱ የትግራይ ሕዝብ ከነርሱ ጋር እንዲቆም ቅስቀሳ ያደርጉበታል። ስለዚህ ሕዋሃቶች በሄዱበት ጎዳና እንዳትሄዱ ካለን ልምድና ተመክሮ ለማሳሰብ እንወዳለን::>>በማለት ለቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ አሣስበዋል።
እንደ ትግራይ ተወላጆቹ መግለጫ፤በ አሁኑ ጊዜ ሕወሃት ወታደራዊ ተቋም ውስጥ ሲያገልግሉ የነበሩትን አባላቶቹን ወደ ውጭ አገር ለስለላ ልኳል::
እነዚህ የሕወሃት ሰላዮች ባረፉበት ቦታ ሁሉ የመኖሪያ ፈቃድ እስኪያገኙ ድረስ ፀረ-ሕወሃት ወሬ እንደሚያወሩ የጠቀሱት የሲያትል ነዋሪዎቹ፤ከዚያም ማን ሕወሃትን እንደሚጠላ ካወቁ በኋላ አንድ ባንድ የግለሰቦቹን ማንነት በያሉበት አገር ላለው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሪፖርት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
<<ዛሬ በዲያስፖራ የሚገኙትን ኢትዮጵያውያን አንድ እንዳይሆኑ የሚከፋፍሉትና የሚለያዩት እነዚህ መንግሥት የላካቸው ሰላዮች ናቸው ናቸው>> ያሉት የትግራይ ተወላጆቹ፤ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ፤ያሉበትን አገርና ስማቸውን ከነማዕረጋቸው በመዘርዘር ለማጋለጥ ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
የህወሀት አባላትና ደጋፊዎች፤ እግዚአብሔር በተለያዬ መንገድ ቢነግራቸውም ካለፈው ስህተታቸው ሊማሩ እንዳልቻሉ አስረድተዋል።
የትግራይ ተወላጆቹ በመጨረሻም በአሁኑ ጊዜ በእስልምና እምነት ተከታዮች ላይ እየተፈፀመ ያለው በደል እንዲቆም አሣስበዋል።
<<ሀይማኖትን ከሀይማኖት፤አንዱን ብሔር ከሌላው ብሔር ማጋጨቱንም እንድታቆሙ በሰፊው የትግራይ ህዝብ ስም እንጠይቃለን>> ሲሉም ተማጽነዋል።