ኢሳት (ሃምሌ 13 ፥ 2008)
የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ታንድ) በጎንደር ህዝብ ላይ የሚፈጸመው ጥቃት እንዲቆም ጥሪ አቀረበ። የህዝብ መብት ጥያቄን ወደብሄር ቅራኔ ለመውሰድ የሚደረገው ሃላፊነት የጎደለው ተግባር እንዲታገድም አሳስቧል።
በዶ/ር አረጋዊ በርሄ የሚመራው የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ታንድ) “ጎንደር የህዝብ ትግል ሲግል፣ የኢህአዴግ ውድቀት ሊቀላጠፍ” በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫ በአሁኑ ወቅት በጎንደር ሰላማዊ ህዝብ ላይ ባጠቃላይ ደግሞ በመላው ኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ግድያና አፈና እናወግዛለን ካለ በኋላ ውግዘት ብቻውን ለውጥ እንደማያመጣም በማመልከት የአምባገነን ቱጃሮችን ስብስብ ለማስወገድ እንታገላለን ሲል ጥሪ አቅርቧል።
“ጭቁኑ የትግራይ ህዝብ እንደማንኛውም ኢትዮጵያ በአምባገነን ቱጃሮች ግፍ እየማቀቁ እንደመሆኑ ሁሉ የተናጥል ትግሉ ጭቆናውን ከጫንቃው እንደወረደለት ጠንቅቆ ያውቃል” በማለት የቀጠለው የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ታንድ) መግልጫ፣ “የትግራይን ህዝብ አምባገነኑን መደብ አጋር አድርጎ የሚያይ ሽባ አመለካከት ከሽባነቱ አልፎ የጋራ ትግሉን አደናቃፊ በመሆኑ አጥብቆ ይቃወማል” በማለትም በሁሉም ወገን ሃላፊነት የተሞላው እንቅስቃሴ እንደሚያስፈልግ አሳስቧል።
“ የኢህአዴግ ገዢ ቱጃሮችን በማንበርከክ የስልጣን ባለቤት ለመሆን የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያደርገውን ትንቅንቅ ለመበረዝ የብሄሮች ቅራኔ በማስመሰል አንዳንድ ቡድኖች ለፕሮፓጋንዳ፣ ለፖለቲካና ለንብረት ፍጆታ ሲሉ ትግሉን ጥላሸት ሊቀቡ የሚዳዱ አደናቃፊዎችም በጊዜ ሃይ ሊሉ ይገባል” ሲል ጥሪ አቅርቧል።
በዶ/ር አረጋዊ በርሄ የሚመራው የትግራይ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ትብብር መግለጫውን ሲያጠቃልል፣ “የጎንደር ህዝብም ይሁን መላው ኢትዮጵያውያዊ የተነሳበትን የፍትህ፣ የአንድነት፣ የሰላም ፍለጋ ትግል ማንም ሊያግደው የማይቻል ማዕከል ነው፣ ስለሆነም ጊዜ ሳይፈጅ ግቡ እንዲመታ በአንድ ሃገራዊ ራዕይ ስር ተሰባስበን እንታገል “የጋራ ጭቆና በጋራ ትግል ይወገዳል፣ የጋራ ሃገር በጋራ ጥረት ይለመልማል” ሲል መግለጫውን አውጥቷል።
የትግራይ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ትብብር (ታንድ) ሊቀመንበር ዶ/ር አረጋዊ በርሄ መግለጫውን በተመለከተ ለኢሳት በሰጡት ቃለምልልስም የትብብርን አስፈላጊነት አጽንዖት ሰጥተዋል፣ ትናንት ኦሮሚያ ላይ የነበረው ሁኔታ ጎንደር ላይ ቀጥሏል ያሉት ዶ/ር አረጋዊ በርሄ፣ ተባብረን እስካልቆየን በሌላውም ይቀጥላል ሲሉ የእንተባበር ጥሪ አስተላልፈዋል።