የትምህርት ስርዓቱ ችግር ከሃያ ስድስት ዓመታት በኋላም እንዳልተስተካከለ መምህራን ተናገሩ፡፡
(ኢሳት ዜና የካቲት 29 ቀን 2010 ዓ/ም) ሰሞኑን በትምህርት ጥራት ዙሪያ መደረግ ስላለበት የማስተካከያ እርምጃ የክልሉን መምህራን እየተዘዋወረ ሲያነጋግር ለነበረው የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አመራር ቡድን አስተያየታቸውን የሰጡት መምህራን፣ በክልሉ ተማሪዎች ዕውቀት ላይ ከፍተኛ ቀልድ እየተፈጸመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የክልሉ ህልውና የተቀመጠው በተማረው የሰው ኃይል ላይ ቢሆንም፣ በየጊዜው የሚወጡ ውጤታማ ያልሆኑ በርካታ የትምህርት አሰጣጥ ፖሊሲዎች መሞከሪያ የሆነው የአማራ ክልል ፣ የተማረ ሰው በማፍራት ከድህነት እንዲወጣ የ ሚያደርገውን ሩጫ የገታ እንደሆነ መምህራኑ በቁጭት ተናግረዋል፡፡
ላለፉት ሃያ ስድስት ዓመታት በክልሉ የተገነቡ የመሰናዶ ትምህርት ቤቶች ቁጥር አነስተኛ መሆኑን የገለጹት መምህር ፣ በአንዳንድ ከተሞች ለፖለቲካ ግብዓት ሲባል በህዝብ የተገነቡ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለሁለት በመክፈል መሰናዶ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ የመሰናዶ ትምህርት ቤቶች ግንባታ በመንግስት እንደሚከናዎን የተቀመጠውን የግንባታ ፖሊሲ በክልሉ እየተፈጸመ አለመሆኑንም መምህሩ አክለዋል፡፡
በተለያዩ የመሰናዶ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን ለማብቃት መምህራን ቢጥሩም ፣በትርፍ ሰዓታቸው የማካካሻ ትምህርት የሚሰጡበት ክፍል በማጣት በወረፋ ለማስተማር መገደዳቸውን የሚገልጹት መምህር፣ ጉዳዩ በክልሉ ተማሪዎች ላይ የተያዘ ትልቅ ቀልድ እንደሆነ ያሰምሩበታል፡፡
የሚታየውን ዕውነታ እንዲስተካከል ህብረተሰቡ በተለያዩ መድረኮች የሚያቀርበውን ተቃውሞ “ጆሮ ዳባ ልበስ” በማለት የማይሰሙት የክልሉ ባለስልጣናት ተማሪዎች በትምህርታቸው ከሌሎች አጎራባች ክልሎች ጋር የተስተካከለ ዕውቀት እንዳይኖራቸው ሆን ተብሎ የሚሰራ ደባ መሆኑን መምህራኑ ይናገራሉ፡፡
በአሁኑ ሰዓት በሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤቶች ከሚገኙ ተማሪዎች መካከል ከመቶ አንድ በላይ በጥሩ ዕውቀት ደረጃ ላይ የማይገኙበትን ሚስጥር የገለጹት ቅሬታ አቅራቢ አብዛኛው ተማሪዎች ስማቸውን በአግባቡ የማይጽፉ ፣በአጥር የሚዘሉ ፣ጠላ ቤት ና ጫት ቤት የሚውሉ እንዲሁም መምህራቸውን የሚደበድቡ ወጣቶች አይበዙም ነበር፡፡
በአንደኛ እና ሁለተኛ ዲግሪ በመመረቅ በተለያዩ መሰናዶ ትምህርት ቤቶች በማስተማር ላይ የሚገኙ መምህራንም፣ ተገቢውን እውቀት ክህሎት አልባ በመሆን ትውልዱን ለመግደል ሌላ መሳሪያ በመሆን በትምህርት ላይ እየተቀለደ መሆኑ ማሳያ መሆኑን በምሬት ያናገራሉ፡፡የገዥወው መንግስት የአማራ ክልል ህዝብ ከድህነት ለመውጣት የሚያደርገውን ጥረት ለማገዝ በፍጹም ፍላጎት እንደሌለው በግልጽ የሚታይ መሆኑን አብራርተዋል፡፡