ሰኔ ፳፩ ( ሃያ አንድ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የቀድሞው የደቡብ ክልል ፕሬዚዳንት የነበሩት አሁን ትምህርት ሚኒስቴርን የሚመሩት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ እና ጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ በሙስና መዘፈቃቸውን በተመለከተ ኢሳት መረጃዎችን ማውጣቱን ተከትሎ፣ የክልሉ ነዋሪዎች በተለይ የአቶ ሽፈራውን የሙስና ሰንሰለት የሚያሳዩ መረጃዎችን እየላኩ ነው።
አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ሰው የአቶ ሽፈራው የሙስና ሰንሰለት እስከ ወረዳ የተዘረጋ ነው ይላሉ። አቶ ሽፈራው ባለቤታቸው የአክሲዮን ድርሻ ባላቸው ይርጋለም ኮንስትራክሽን አማካኝነት በክልሉ የተለያዩ ጫረታዎችን እያሸነፉና ከደረጃ በታች የሆኑ ስራዎችን እያቀረቡ ገንዘብ ይዘርፋሉ። የአላባ ወረዳን በምሳሌነት የጠቀሱት ግለሰቡ፣ በወረዳው የተገነባው ዲስትሪክ ሆስፒታል ያለምንም ጫረታ ይርጋለም ኮንስትራክሽን በ27 ሚሊዮን ብር እንዲሰራው ተደርጓል ብለዋል።
የግንባታው ንድፍ ሲወጣ የጣራው ብረት መጠን 2.5 ሚ.ሜ መሆን እንዳለበት ቢቀመጥም፣ ከንድፉ ውጭ በ2 ሚ.ሜ እንዲሰራ ተደርጎ 1 ሚሊዮን 500 ሺ ብር ከጣሪያው ብቻ ተበልቶበታል።
ሆስፒታሉ ከመሰረቱ ጀምሮ እስከ ቤቱ ቁመት በግልፅ ጥራቱን ያልጠበቀ እና ከፍተኛ ማጭበርበር የተፈጸመበት ነው ተብሏልም።
የልዩ ወረዳው አስተዳደር ዋና ጽ/ቤትም ያለጫረታ የተገነባው በዚሁ የአቶ ሽፈራው ባለቤት አክሲዮን በያዙበት በይርጋለም ህንፃ ኮንስትራክሽን ድርጅት ሲሆን፣ ይህንን ህንፃ ያለጫረታ እንዲሰራው የሰጡትም የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ኑረዲን ሃሰን ናቸው።
የህንፃው ዲዛይን አጠቃላይ ወጪ በጊዜው በነበረው ዋጋ 14 ሚሊዬን ብር የነበረ ቢሆንም፣ በመጨረሻ የተፈጸመው ክፍያ ግን 21 ሚሊዮን ብር ነው ። የሃላባ ቁሊቶ ከተማ የጋራ ቢሮንም እንዲሁ የይርጋለም ህንፃ ኮንስትራክሽን ያለ ጨረታ ወስዶ የሰራው ሲሆን፣ ለዚሁም ግንባታ የተጋነነ ወጪ ተከፍሏል።
በአቶ ሽፈራው ባለቤትና በወረዳው አስተዳዳሪ በአቶ ኑረዲን ሃሰን የተፈጠረው ከፍተኛ የጥቅም ትስስር ለአርሶአደሩ በሚሰጠው ማዳበሪያም ላይ ተዘርግቷል። አቶ ሽፈራው የዘረጉት የሙስና መረብ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍንንም እንደሚያካትት ምንጮች ይገልጻሉ።