የታገቱትን ሕጻናት ለማስለቀቅ የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስዱ ተመድ አሳሰበ

ግንቦት ፲፰ (አሥራ ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ሁለት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ኤክስፐርቶች ባለፈው ሚያዝያ ወር ላይ በሙርሌ ጎሳ አባላት ታግተው የተወሰዱት ሕጻናት ካለምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናኙ የደቡብ ሱዳንና የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጊዜ ሳይወስዱ የልጆቹን መመለስ ማፋጠን እንዳለባቸው አሳሰቡ።
በጋምቤላዋ ጂካውና ላሬ ወረዳዎች13 የኑዌር መንደሮች ላይ ጥቃት ተፈጽሟል። ከ208 በላይ የሚሆኑ ሴቶችና ሕጻናት ሲገደሉ ከ80 በላይ የሚሆኑት ከባድና ቀላል የመቁሰል አደጋ ሲደርስባቸው ከ146 በላይ የሚሆኑ ልጃገረዶችና ታዳጊ ሕጻናት መታገታቸውንና ቁጥራቸው ከ2 ሽህ በላይ የሚሆኑ የቀንድ ከብቶች መዘረፋቸውን ድርጅቱ አስታውቋል። ይህንን ኢሰብዓዊ ድርጊት በአፋጣኝ እልባት ሊበጅለትና ልጆቹ ወደ ቤተሰቦቻቸው ይመለሱ ይገባል ሲሉ ሪፓርታቸውን አቅርበዋል።
በድርጅቱ የጥናት ዘገባ መሰረትም የታገቱት ሕጻናት እድሜያቸው ከ13 ዓመት በታች መሆናቸውንና ከእነዚህ ውስጥ ባለፉት ሳምንታት ውስጥ 59 የሚሆኑት ታጋቾች ወደ አገራቸው ተመልሰዋል። ሕጻናትን አግቶ ለሽያጭ ማዋል በቀጠናው ተባብሶ ያለ ነውረኛ ድርጊት ሲሆን የሁለቱ አገራት ባለስልጣናት በድርድር እልባት ሊያበጁለት ይገባል ብለዋል። ሕጻናቱን ከታገቱበት ማስመለስ ብቻ ሳይሆን ወደ ሕብረተሰቡ ሲመለሱ ለማኅበረሱቡ የመልሶ ማቋቋም የአቅም ግንባታና እንዲህ ዓይነት ድርጊቶች እንዳይግደገሙና የጥቃት መከላከያ መላ ሊበጅለት ይገባል ሲሉ መክረዋል። ደቡብ ሱዳንና ኢትዮጵያ ለሰብዓዊ መብት መከበር ለእያንዳንዱ ግለሰብ ሕይወት የደኅንነት ዋስትና ሊሰጡ ይገባቸዋል ሲሊም በአጽንኦት አሳስበዋል።
ልጆቻቸው የታገቱባቸው ወላጆች ከፍተኛ በስነልቦናዊ ጫና ውስጥ ያሉ ሲሆን ታግተው ከተወሰዱባቸው ሁለት ልጆቻቸው አንዱ የተመለሰላቸው እናት ሲናገሩ ”ቀንና ሌሊት በስጋትና በጭንቀት ውስጥ ነኝ። ዳግም ተመልሶ አገኘዋለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር። አንዱ ልጄ በመመለሱ ደስተኛ ነኝ። አሁንም ቀሪውን ልጄን በተስፋ እጠብቃለሁ” ብለዋል።