የታንዛኒያ ፖሊስ በህገወጥ ገብተዋል የተባሉ 66 ኢትዮጵያውያንን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ

ኢሳት (ሚያዚያ 9 ፥ 2009)

የታንዛኒያ ፖሊስ ወደ ሃገሪቱ በህገ-ወጥ መንገድ ገብተዋል የተባሉ 66 ኢትዮጵያውያን በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታወቀ።

ስደተኛ ኢትዮጵያውያኑ በአንድ ተሽከርካሪ ሆነው በመጓጓዝ ላይ እንዳሉ ከነዋሪዎች በደረሰ ጥቆማ በጸጥታ አባላት ሊያዙ መቻላቸውን ዘ-ሲቲዝን የተሰኘ የታንዛኒያ ጋዜጣ ሰኞ ዘግቧል።

የሃገሪቱ የኢሚግሬሽን መምሪያ በበኩሉ በተለያዩ ጊዜያው ወደ ታንዛኒያ በህገ-ወጥ የሚገቡ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን አስታውቀዋል።

የምቤያ አስተዳደር ፖሊስ ኮማንደር የሆኑት ዳሂር ኪዳቫሻሪ ኢትዮጵያውያኑ ወደ ጎረቤት ማላዊ የመጓዝ እቅድ እንደነበራቸው ለመገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።

በተያዘው አመት በአንድ ዘመቻ ይህን ያህል ቁጥር ያለው ስደተኛ በቁጥጥር ስር ሲውል ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ያሉት የፖሊስ ሃላፊው፣ ስደተኛ ኢትዮጵያውያኑ በፖሊስ ምርመራ እየተካሄደባቸው እንደሚገኝ አክለው ገልጸዋል።

በስደተኞቹ ላይ የሚካሄደው ምርመራ እንደተጠናቀቀም ሃገሪቱ በህገወጥ መንገድ ገብተዋል የተባሉ ኢትዮጵያውያን ለፍርድ እንደሚቀርቡ ተገልጿል።

በታንዛኒያ እንዲሁም በጎረቤት ማላዊ በህገወጥ መንገድ ወደ ሃገሪቱ ገብታችኋል የተባሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በእስር ላይ እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የአለም አቀፍ ስደተኞች ድርጅት (IOM) በበኩሉ በደቡባዊ የአፍሪካ ሃገራት በተለያዩ እስር ቤቶች የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሃገራቸው ለመመለስ የገንዘብ እጥረት እንዳጋጠመው ገልጿል።

የማላዊ መንግስት በበኩሉ የእስር ቅጣታቸውን የጨረሱ ከ120 በላይ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን የበጀት እጥረት በመኖሩ ወደ ሃገራቸው ሊመለሱ እንዳልቻሉ ለሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ሲገልፁ ቆይተዋል።

የማላዊ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በሶስት እስር ቤቶች የሚገኙት ኢትዮጵያውያን በከፍተኛ የምግብ ዕጥረትና በበሽታ እየተሰቃዩ እንደሆነ በመግለጽ የሃገሪቱ መንግስት ኢትዮጵያውያኑን ወደ ሃገራቸው እንዲመልስ ጥሪን አቅርበዋል።

ከአንድ አመት በፊት በኦሮሚያ የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ ኢትዮጵያዊ ወደ ተለያዩ ሃገራት እየተሰደዱ መሆኑን የአለም አቀፍ ስደተኞች ድርጅት ይገልጻል።

መንግስት በበኩሉ የስደተኞቹን ፍስልሰት ለመቆጣጠር በድንበር ዙሪያ የጸጥታው ቁጥጥር ቢጠናከርም ችግሩ አሁንም ድረስ ሊፈታ አለመቻሉን አስታውቋል።