ሰኔ ፳፰ (ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የታሰሩት የዋልድባ መነኮሳት ለነዋሪው ተቃውሞ፣ ለተቃጠለው የስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክት ዶዘር እና በተቃውሞው ለተጎዱት ሠራተኞች ሀላፊነት እንዲወስዱ እየተገደዱ መሆናቸውን ደጀ-ሰላም ዘገበ።
ደጀ-ሰላም ከስፍራው የሚገኙ ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ባለፈው ሳምንት፣ ሰኔ 23 ቀን 2004 ዓ.ም÷ ከቀኑ ሰባት ሰዓት ላይ ከዋልድባ ሰቋር ኪዳነ ምሕረት ገዳም የተወሰዱት አምስት መነኰሳት ፤በዓዲ አርቃይ ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ በአንድ ቆርቆሮ ቤት ውስጥ እንደታሰሩ ይገኛሉ።
በተጠቀሰው ቀን በአራት ያህል ቶዮታ መኪናዎች በዓዲ አርቃይ ወረዳ ጸጥታ ሓላፊዎች እና በፌዴራል ፖሊስ ኀይሎች ከገዳሙ ከተወሰዱት አምስት መነኰሳት መካከል ፤ አባ ተክለ ሃይማኖት እና አባ ኀይለ ሥላሴ የተባሉት ሁለቱ ወደ ዓዲ አርቃይ፤ አባ ገብረ ማርያም ፣ አባ ኀይለ ኢየሱስ እና አባ ገብረ እግዚአብሔር የተባሉት ሦስቱ ደግሞ በመጀመሪያ ወደ ማይ ፀብሪ ፤ በኋላም ወደ ዓዲ አርቃይ መመለሳቸው ታውቋል፡፡
ድረ-ገጹ እንዳለው፤ በአሁኑ ወቅት አምስቱም መነኰሳት በዓዲ አርቃይ ፖሊስ ጣቢያ በሚገኝ አንድ ቆርቆሮ ቤት ውስጥ ሌላ ሰው ሊጠይቃቸው በማይችልበት ኹኔታ ተቆልፎባቸው ይገኛሉ።
አምስቱ መነኰሳት ለእስር በተዳረጉበት ሁኔታ ላይ የማይ ፀብሪ ወረዳ አስተዳደር ከዓዲ አርቃይ ወረዳ አስተዳደር ጋራ ውዝግብ ውስጥ መግባታቸውም ተሰምቷል፡፡
የውዝግቡ መንሥኤ፤ አምስቱ መነኰሳት የተወሰዱበት የዋልድባ ሰቋር ኪዳነ ምሕረት ገዳም- በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን የሚገኝ ከመሆኑ አኳያ፤ በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ክልል ወደሚገኘው ማይ ፀብሪ ተወስደው በመታሰራቸው ላይ ሓላፊነት ላለመውሰድ ነው ተብሏል፡፡
የዓዲ አርቃይ ወረዳ የፍትሕና ጸጥታ ዘርፍ ሓላፊ፦ ‹‹ሓላፊነታቸውን በአግባቡ አልተወጡም›› በሚል ወደ ሲቪል ሰርቪስ እንዲዘዋወሩ መደረጉን የጠቀሱት ምንጮች፤ የዝውውሩ ምክንያት ከዚሁ ውዝግብ ጋራ ሳይያያዝ እንደማይቀር ያላቸውን ግምት ጨምረው ገልጸዋል፡፡
‹‹ሕዝብን ለተቃውሞ ቀስቅሰዋል፤ ከውጭ ሚዲያዎች ጋራ ይገናኛሉ›› በሚል እየተዋከቡ ከሚገኙት ከወንድና ሴት የገዳሙ ማኅበረ መነኰሳት መካከል÷ ቅዳሜ ዕለት የተወሰዱት አምስት መነኰሳት÷ ባለፈው ሳምንት አጋማሽ የዛሬማ ወንዝ ግድብ በሚሠራበት የፕሮጀክቱ ስፍራ ላይ ለተቃጠለው ዶዘርና ለተጎዱት የፕሮጀክቱ ሠራተኞች ‹‹ሓላፊነቱን ውሰዱ›› የሚል ጫና በጸጥታ ኀይሎች እየተደረገባቸው መኾኑን ምንጮቹ ገልጸዋል፡፡
አምስቱ መነኰሳት ሰኔ ሰባት ቀን 2004 ዓ.ም በዛሬማ ቀበሌ፤ ከአካባቢው አመራሮች ጋራ ስለ ስኳር ልማት ፕሮጀክቱ ግንባታ ተደርጎ በነበረው ስብሰባ ተገኝተው ነበር።
የዜናው ምንጮች ጨምረው እንዳመለከቱት÷ ፕሮጀክቱ በዋልድባ ገዳም ህልውናና ክብር ላይ ከሚያደርሰው ተጨባጭና ታሳቢ ስጋቶች የተነሣ በአካባቢው የተቀሰቀሰው ተቃውሞ በያዝነው ሳምንትም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide