የታላቁ ሩጫ ውድድር በከፍተኛ ወታደራዊ ጥበቃና አጀብ ተካሄደ

ህዳር ፲፮(አስ ስድስት )ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :-የታላቁ ሩጫ በከፍተኛ ወታደራዊ ጥበቃ ሥር ሆኖ እሁድ ህዳር 15 ቀን 2006 ዓ.ም ተካሂዷል፡፡

መነሻውን ጃንሜዳ በማድረግ ፥ በ6 ኪሎ አደባባይ ፣ በምኒሊክ ሆስፒታል፣ በቀበና ፣በ አቧሬ ፣ በእንግሊዝ ኤምባሲ ፣ በመገናኛ አደባባይ በማደረግ ተመልሶ ጃንሜዳ የተጠናቀቀው ይህ ለ 13ኛ ጊዜ የተካሄደው ውድድር ከወትሮው በተለየ ጥበቃና የፖሊስ ተደጋጋሚ ፍተሻ በመታጀብ ነበር፡፡

ቅዳሜ የህጻናት የታላቁ ሩጫ ውድድር ለማካሄድ መርሃግብር ወጥቶለት ዝግጅቱ ሊካሄድ ጥቂት የመጨረሻዎቹ ሰዓታት ላይ  የሽብር ጥቃት ይፈጸማል በሚል መሰረዙም ታውቆአል፡፡

እሁድ ማለዳ ሪፖርተራችን ተዘዋውሮ በተመለከታቸው በተለይ ከአራት ኪሎና በስድስት ኪሎ የመጡ ተሳታፊዎች በሶስት የተለያዩ ስፍራዎች ተደጋጋሚ ፍተሻዎች የተደረገባቸው ሲሆን በተለይ የተለያዩ ድርጅቶች ዓርማዎችንና ሌሎች አልባሳት የያዙ ተወዳዳሪዎች ወደውድድሩ ቦታ ለማለፍ ከፍተኛ ችግር ገጥሞአቸው ታይቷል፡

ሰማያዊ ፓርቲ በዚህ ውድድር ላይ ጥቁር ልብስ በመልበስ በሳዑዲዓረቢያ በወገኖቻችን ላይ የደረሰውን ችግር ሕዝቡ እንዲቃወም ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ ፖሊሶች በተለይ ጥቁር አልባሳት ያደረጉ ሰዎችን ልብስ ሲያስወልቁ ታይተዋል፡፡

በተጨማሪም ከስድስት ኪሎ ውድድሩ እስከሚጀመርበት ጃንሜዳ ድረስ የሚገኙ ማናቸውም የንግድ ሱቆች፣ መኖሪያ ቤቶች፣የተለያዩ ቢሮዎች፣የህክምና ማዕከላትና የመሳሰሉት እንዲዘጉ በፖሊሶች በመገደዳቸው ተወዳዳሪዎች ከመደብሮች ውሃና ለስላሳ መጠጦችን ለመግዛት ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡

ከ37 ሺህ በላይ አንጋፋና ታዋቂ አትሌቶችን ጨምሮ የግል ተወዳዳሪዎች ተካፋይ የሆኑበት ይህው ውድድር በፖሊስ በኩል የተፈራው የሽብር ጥቃት ሳይገጥመው በሰላም ተጠናቆአል።