(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 29/2010) በኢትዮጵያ የተፈጠረውን ሁኔታ ለማደፍረስ የሚደረጉ ሙከራዎች የትም የማይደርሱ፣መንግስት የሚያውቃቸውና የሚቀጣቸው ናቸው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ገለጹ።
እነዚህ ርምጃዎች ባዶ ፍላጎቶች እንጂ ለውጥን ማቆም የሚችሉ አይደሉም ብለዋል።
በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ጥሪ አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን የተናገሩት ዛሬ በፓርላማ ቀርበው የ2011 በጀት ላይ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው።
ለቀጣዩ በጀት አመት ዛሬ 346 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በጸደቀበት የፓርላማው ስብሰባ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የበጀቱ አብዛኛው ክፍል ማለትም 64 በመቶ ድሆችን ታሳቢ ያደረገና በድህነት ቅነሳ ላይ የሚያተኩር እንደሆነም ተናግረዋል።
ከአጠቃላይ በጀቱ 55 በመቶ ለካፒታል በጀት የተመደበ ቢሆንም በዚህ አመት አዳዲስ ፕሮጀክቶች እንደማይኖሩ ግልጽ አድርገዋል።
የተጀመሩትን ፕሮጀክቶች ለማስጨረስ 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
ይህ ባለበት ሁኔታ ተጨማሪ ፕሮጀክት መጀመሩ ተገቢ እንዳልሆነ በግልጽ አስቀምጠዋል።
የተጀመሩት ፕሮጀክቶች ማለት ያልቻሉት በገንዘብ ችግር ብቻ ሳይሆን በብቃትና በእውቀት ማነስ ጭምር እንደሆነም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
ለታዳጊ ክልሎች የሚሰጡት ድጋፍ ወደ 16 በመቶ ከፍ ማለቱንም ከማብራሪያቸው መገንዘብ ተችሏል።
አዳዲስ ፕሮጀክት ማቀድ ለተጨማሪ ብክነት ያጋልጠናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አንዳንዶቹ ፕሮጀክቶች ያለባቸው እቃ ከአጠቃላይ አቅማቸው በላይ እንደሆነም አስረድተዋል።
ለፕሮጀክቶቹ የተወሰደው የሃገር ውስጥ ብድር ከ400 ቢሊየን ብር በላይ መሆኑንም አስታውቀዋል።–የውጭ ብድሩን ግን አልጠቀሱም።
መንግስት ከ7 አመት በፊት ባቀደው የትራንስፎርሜሽን እቅድ ሃገሪቱ ከወጭ ንግድ ዘንድሮ ማግኘት የሚገባት 10 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ነው።
ነገር ግን አሁን ላይ የእቅዱ አንድ ሶስተኛ ላይ ነን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በውጭ ምንዛሪ ረገድ ያለው ክፍተትን ለመሙላት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እገዛ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በዚህም ወደ ሃገር ቤት የሚልኩትን ገንዘብ በባንክ አማካኝነት እንዲልኩ፣እንዲሁም ከእለት የቡና ወጪያቸው አንድ ዶላር በማዋጣት በሃገር ቤት ለሚሰሩ የትምህርትና የድህነት ቅነሳ ወጪዎች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
በሃገር ቤት ያሉ ነጋዴዎችም ገንዘብ በቤታቸው እያከማቹ መሆናቸውን የገለጹትና የሚሊየን ብር ግብይቶችን ቤታቸው ባከማቹት ካሽ እየፈጸሙ መሆናቸውን ተችተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ መንግስት ወደ ርምጃ ከመግባቱ በፊት ህጋዊውን የባንክ አሰራር እንዲጠቀሙ አሳስበዋል።
ወጣቶችም በውሃ ቀጠነ ወደ ሃይልና አመጽ እንዳይገቡ መክረዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘም ሃገሪቱ ውስጥ የተፈጠረውን ሁኔታ ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ ወገኖችም የትም እንደማይደርሱ አስጠንቅቀዋል።
እነዚህ ርምጃዎች ባዶ ፍላጎቶች እንጂ ለውጥን ማቆም የሚችሉ አይደሉም ሲሉም አክለዋል።
ፖለቲከኞች አንዱ በሽታቸው ነገር ሲድንና ሲሞት አለመለየታቸው ነው በማለት ራሳቸውን ከሁኔታዎች ጋር ማስማማት ያቃታቸውን ተችተዋል።
ይህ መጓተት ግን ለውጡን አያቆመውም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናግረዋል።