(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 6/2011)ከማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች የተፈናቀሉ 46 ሺህ የሚሆኑ ተፈናቃዮች መንግስት በቂ የሆነ የምግብ እና ቁሳቁስ ድጋፍ እያቀረበላቸው አለመሆኑን ገለጹ።
በሁለቱ ዞኖች በተከሰተው የፀጥታ ችግር ምክንያት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች መንግስት በቂ የሆነ የምግብ ፣የውሃ ፣የጤና እና ቁሳቁስ ድጋፍ እያቀረበላቸው አለመሆኑን ገልጸዋል ።
በአካባቢው ያለው ሁኔታ አሁንም የተረጋጋ አለመሆኑ ይነገራል።
ይሕ በእንዲህ እንዳለም በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ የነበሩ 43 ክላሽሸንኮቭ የጦር መሳሪያዎችና 1 ሺህ 300 ጥይቶች በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን የአማራ ክልል ፖሊስ አስታውቋል።
ከማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች በተለይም በሳንጃ፣አይምባ ፣ትክል ድንጋይና ጭልጋ የሚገኙ 46 ሺህ የሚሆኑ ተፈናቃዮች በመንግስት በኩል ምንም ድጋፍ እንዳላገኙ ገልጸዋል።
የአማራ ክልል የአደጋ መከላከል ምግብና ዋስትና ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ግን ተፈናቃዮች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ገልጿል።
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ተከማችቶ የነበረን 600 ኩንታል የምግብ እህል ለተጎጂዎች ለማዳረስ እየተጓጓዘ መሆኑን በመጠቆም ።
ከዚህ በፊት በአካባቢው ተከስቶ በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት አቅርቦቱን ለተጎጂዎች በተፈለገው ጊዜና ሰዓት ማድረስ እንዳላስቻለም ተናግረዋል።
በቀጣይም ችግሩ እንዳይፈጠር የክልሉና የፌዴራል መንግስት በጋራ እና በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
የፌዴራል መንግስት በክልሉ ለሚገኙ ሁሉም ተፈናቃዮች 13 ሺህ ኩንታል የምግብ እህል ድጋፍ ማድረጉ ታውቋል ።
የአማራ ክልል መንግስት ደግሞ 5 ሺህ ኩንታል የምግብ እህል ገዝቶ በማከፋፈል ላይ መሆኑ ቢገለጽም ከማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች የተፈናቀሉት ዜጎች ግን ምንም አይነት እርዳታ አልደረሰንም ብለዋል።
የፌደራልና የክልሉ መንግስት አካባቢውን ሰላም ለማድረግ እየሰሩ ነው ቢባልም በአካባቢው ያለው ሁኔታ ግን አሁንም የተረጋጋ አለመሆኑን ነው የኢሳት ምንጮች የሚናገሩት።
ይሕ በእንዲህ እንዳለም በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ የነበሩ 43 ክላሽሸንኮቭ የጦር መሳሪያዎችና 1 ሺህ 300 ጥይቶችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአማራ ክልል ፖሊስ አስታውቋል።
የጦር መሳሪያዎቹን ከጋምቤላ ወደ አማራ ክልል ጎንደር ከተማ በኤፍ ኤስ አር የጭነት ተሽከርካሪ ለማስገባት ሲሞክሩ ተይዘዋል።
መኪናው ሲያሽከረክር የነበረው አሽከርካሪም በቁጥጥር ሥር መዋሉን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ገልጿል።
በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ የነበሩ የጦር መሳሪያዎች ላይ ተጨማሪ የምርመራ ሥራ እያከናወነ መሆኑንም ኮሚሽኑ ገልጿል።