(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 19/2010) ከሕገ መንግስታዊ ስርአት ውጪ የተፈናቀሉና የተሰደዱ ዜጎች ካሳ ተከፍሏቸው ወደ ቀድሞ ቦታቸው እንዲመለሱ መድረክ አሳሰበ።
በማፈናቀሉ ሒደት የተሳተፉ አካላትም እስካሁን ተጠያቂ አለመሆናቸውን መግለጫው አስገንዝቧል።
በኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ/ኦፌኮ/፣ አረና ትግራይ ለዲሞክራሲና ሉአላዊነት/አረና/፣Yeኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ/ኢሶዴፓ/ እና የሲዳማ አርነት ንቅናቄ/ሲአን/ ፓርቲዎች ስብስብ የሆነው መድረክ ትላንት ጋዜጣዊ መግለጫውን ሰጥቷል።
መድረክ በዚህ መግለጫው መንግስት በህገወጥ መንገድ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ማያውቋቸው አካባቢዎች ወስዶ ለማስፈር ማቀዱ የሃገሪቱን አንድነትም ሆነ የሕዝቡን አብሮነት አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን አስታውቋል።
እንደዚህ አይነት የመንግስት ርምጃዎች በቀጠሉ ቁጥር ዜጎች በኢትዮጵያዊነት ተከብረው በፈለጉት አካባቢ ተንቀሳቅሰው የመኖር ሕገ መንግስታዊ መብት ከማጣሱም በላይ ሃገራዊ አንድነትን የመገንባት ሂደት አደጋ ላይ የጣለ መሆኑን አሳስቧል።
በመሆኑም መንግስት ህገወጥ በሆነ መንገድ የተፈናቀሉና የተሰደዱ ዜጎችን በማያዉቁት አካባቢ ለማስፈር የጀመረውን እንቅስቃሴ ማቆም ይኖርበታል ብሏል።
መንግስት የተፈናቀሉትን ዜጎች ተገቢውን ካሳ ከፍሎ ወደ ቀያቸው በመመለስ የማቋቋም ስራ እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል።
በማፈናቀሉ ሒደት የተሳተፉ የፌደራልና የክልል ባለስልጣናት በሕግ ፊት ይቀርባሉ ተብሎ በመንግስት የተነገረው ከንግግር ያልዘለለ መሆኑ መድረክን አሳዝኖታል ብሏል።
ስለሆነም ባለስልጣናቱ በሕግ ፊት ቀርበው አስፈላጊው ርምጃ መወሰድ እንዳለበት አሳስቧል።
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ /ኦፌኮ/ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች መካከል በተፈጠረው ያለመስማማት የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ አለማድረግ ሃገራዊ አንድነቱን እንደሚያናጋ ለኢሳት መግለጻቸው የሚታወስ ነው።