(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 7/2010)
በኦሮሚያ ክልል የተጀመረው አድማና የተቃውሞ ሰልፍ ለ3ኛ ቀን መቀጠሉ ታውቋል።
በወሊሶ፣ ነቀምት፣ አዳማ፣ አወዳይ፣ አዲስ አበባ ዙሪያና ሌሎች በርካታ አከባቢዎች በሶስተኛው ቀን ተቃውሞ ተሳታፊ ሆነዋል።
በወሊሶ ዛሬ በተካሄደው ትዕይንተ ህዝብ በስልጣን ላይ ያለው የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር ሕወሃት መንግስት ላይ ተቃውሞ ተሰምቷል።
ዛሬም በወሊሶ ሱቆችና መደብሮች እንደተዘጉ ነው።
በነቀምት ወለጋ በሶስተኛ ቀን የተቃውሞ እንቅስቃሴ ሕዝቡ አደባባይ በመውጣት ለተፈቱት የኦሮሞ ፌደራሊስት አመራሮች ደስታውን ገልጿል።
ዛሬ አዳማ ናዝሬት የስራ ማቆም አድማና የተቃውሞ ሰልፍ እንደተደረገም ለማወቅ ተችሏል።
ወሊሶ፣ ነቀምት፣ አዳማ፣ አወዳይ፣ አዲስ አበባ ዙሪያና ሌሎች በርካታ አካባቢዎች በሶስተኛው ቀን ተቃውሞ ተሳታፊ መሆናቸው ታውቋል።
ትላንት ምሽት አቶ በቀለ ገርባን በክብር የተቀበሉት የአዳማ ነዋሪዎች ዛሬ ተቃውሞአቸውን በመቀጠል የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር ሕወሃት ከስልጣን እንዲለቅ ጠይቀዋል።
በጉሮ ባሌ ተቃውሞ የተካሄደ ሲሆን ሁለት ተሽከርካሪዎች መቃጠላቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በአወዳይም ሕዝቡ አደባባይ ወጥቶ ተቃውሞውን አሰምቷል።
በአርሲ አንዳንድ ከተሞች አድማው ቀጥሏል።
በአዲስ አበባ ሰበታ ዙሪያ ተቃውሞ መደረጉም ታውቋል።