የተወሰኑ ፓርቲዎች የምርጫ ቦርድን ስብሰባ ረግጠው ወጡ

ጥቅምት ፯(ሰባት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በጊዜ ሰሌዳ ላይ ለመወያየት ምርጫ ቦርድ በጊዮን ሆቴል የጠራውን ስብሰባ ‹‹ጥያቄዎቻችን የሚመልስ አይደለም›› በሚል ሰማያዊ ፓርቲ ፣ የመላው ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (መኢዴፓ) እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት

ፓርቲ (ኢብአፓ) ተወካዮች ረግጠው መውጣታቸውን ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል፡፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት ፓርቲ (ኢብአፓ) ዋና ጸኃፊ ወ/ት መሊሃ ጀሃድ  ምርጫ ቦርድ እነሱ ላነሱት ጥያቄ ሌላ ጊዜ እንደሚመለስበትና በቅድሚያ በጊዜ ሰሌዳው ላይ መነጋገር እንዳለባቸው በማሳወቁ ስብሰባውን ረግጠው ለመውጣት መገደዳቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል።

12 ፓርቲዎች ምርጫ ቦርድ ከምርጫ ንግግር በፊት ለነጻና ፍትሃዊ ምርጫ የሚያበቁ ሁኔታዎችን እንዲያመቻች ለማድረግ ውይይት እንዲጀምር መጠየቃቸው ይታወሳል።