የተከዜ ሃይል ማመንጫ ሶስት ተርባይኖች ስራ ማቆማቸው ተገለጸ

ኢሳት (ጥቅምት 29 ፥ 2009)

ከስምንት አመት በፊት በ360 ሚሊዮን ዶላር የተገነባው የተከዜ ሃይል ማመንጫ ግድብ አጋጥሞታል በተባለ የቴክኒክ ችግር ከአራት ተርባይኖች ሶስቱ ስራ ማቆማቸው ተገለጸ።

የሃይል ማመንጫ ጣቢያው ባለፈው አመት በድርቅ ምክንያት የውሃ እጥረት አጋጥሞት የነበረ ቢሆንም፣ ግድቡ ያለ በቂ ውሃ የኤሌክትሪክ ሃይል እንዲያመነጭ በመደረጉ በተርባይኖች ላይ የመሰንጠቅ አደጋ እንደደረሰ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ማክሰኞች አስታወቀ።

300 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ሃይል ሲያመነጭ የነበረው ይኸው ጣቢያ አጋጥሞታል በተባለው ብልሽት ምክንያት በአሁኑ ሰዓት 45 ሜጋ ዋት ብቻ እያመነጨ መሆኑ ታውቋል።

ከስምንት አመት በፊት ከ360 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ተደርጎበት የነበረው የተከዜ የሃይል ማመንጫ ሃገሪቱ ካሉት ጠቅላላ ሃይል ሶስት በመቶ የሚሆነውን ይሸፍን እንደነበር የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ገልጿል።

75 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ሃይል የማመንጫ አቅም ያለው እና በአሁኑ ሰዓት በብቸኝነት ሃይል እያመነጨ ያለው አንደኛው ተርባይን በአማካይ ከ45 እስከ 55 ሜጋ ዋት ብቻ እያመነጨ መሆኑም ተነግሯል።

የሃይል ማመንጫው ያጋጠመውን የቴክኒክ ብልሽት እልባት ለመስጠት ከአንድ ኩባንያ ጋር የ215ሺ ዶላር ስምምነት መፈረሙን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

የተከዜ ሃይል መመንጫ ጣቢያ እስከ 250 ሜጋ ዋት የሚደርስ ሃይል ማመንጨት በማቆሙ በአካባቢው የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማድረጉም ታውቋል።

የሃይል ማመንጫ ጣቢያው ቀድሞ ከተያዘለት በጀት የ136 ሚሊዮን ዶላር ጭማሪን አስመዝግቦ የነበረ ሲሆን፣ ባለሙያዎች ግድቡ የተያዝለትን በጀትና ጂኦግራፊያዊ አቀማመጡ አዋጭ እንዳልሆነ ሲገልፁ መቆየታቸው የሚታወስ ነው።

አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ የክልል ከተሞች የሚገኙ ነዋሪዎችና የፋብሪካ ባለንብረቶች በኤሌክትሪክ ሃይል መቆራረጥና እጥረት ምክንያት ለችግር መዳረጋቸውን ይገልጻሉ።

250 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት ያቆመውና በትግራይ ክልል የሚገኘው የተከዜ ሃይል ማመንጫ ግድብ መቼ ወደ ሙሉ አቅሙ እንደሚመለስ የታወቀ ነገር የለም።