የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ በሸንኮራ አገዳ ምርት እጥረት ወደ ስራ አለመግባቱ ተገለጸ

ኢሳት (ሚያዚያ 18 ፥ 2009)

ከሁለት አመት በፊት ስኳርን ለውጭ ገበያ ያቀርባል ተብሎ የነበረውና ግንባታው በቅርቡ የተጠናቀቀው የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ በሸንኮራ አገዳ ምርት እጥረት ወደ ስራ አለመግባቱ ተገለጸ።

ይኸው ከህንድ መንግስት በተገኘ ብድርና ከሃገር ውስጥ የመንግስት በጀት የተቋቋመው የስኳር ፋብሪካ ኣጋጥሞታል የተባለው የምርት አቅርቦት እስከቀጣዩ አራት አመት ድረስ የሚዘልቅ መሆኑም ታውቋል።

የፋብሪካውን ሁኔታ አስመልክቶ ሪፖርትን ለፓርላማ ያቀረበው የመንግስት የልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለፋብሪካው የተዘጋጀው የሸንኮራ አገዳ ፋብሪካው ተገንብቶ ከመጠናቀቁ በፊት ቀድሞ በመድረሱ ለምርት የማይሆን በመሆኑ ወደ ስራ ሊገባ አለመቻሉን እንደገለጸ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ከተያዘለት በጀት እና ጊዜ በላይ የወሰደው የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ በስራ ላይ ለሌሉ 1ሺ 577 ሰዎች ደመወዝ እየከፈለ መሆኑንም ኮሜቴው ለፓርላማ አስረድቷል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በበኩሉ ወደ ስራ መግባት ያልቻለው ፋብሪካ ለማይሰሩ ሰዎች ደመወዝ መክፈሉ የፋብሪካውን ህልውና አደጋ ውስጥ እንደከተተው ገልጾ፥ ድርጊቱን የፈጸሙ አካላት ከተጠያቂነት አያመልጡም ብሏል።

ይሁንና የትኛው የመንግስት አካል የሰራተኞቹ ጉዳት እንደሚመለከተውና ተጠያቂ እንደሚሆን የተገለጸ ነገር የሌለ ሲሆን፣ 1ሺ 557 ይደርሳሉ የተባሉት እና በስራ ላይ የሌሉት ሰራተኞች ለረጅም አመታት ወርሃዊ ደመወዝ ሲከፈላቸው መቆየቱን ለመረዳት ተችሏል።

የሸንኮራ አገዳ ምርት እጥረት አጋጥሞታል የተባለው የተንዳሆን ስኳር ፋብሪካ ከመስከረም 2010 አም በኋላ ወደ ስራ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል። ይኸው ፋብሪካ ምርቱን ከሁለት አመት በፊት ለውጭ ሃገር ገበያ በማቅረብ ሃገሪቱ ከውጭ የምታስገባውን ስኳር እንደሚያስቀርና የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት እንደሚጀምር የስኳር ኮርፖሬሽን ከሁለት አመት በፊት ገልጾ እንደነበር ይታወሳል።

የህንድ መንግስት ለፋብሪካው ግንባታ ይውል ዘንድ የ600 ሚሊዮን ዶላር ብድርን አቅርቦ የነበረ ሲሆን፣ ፋብሪካው ወደ ስራ ሳይገባ ብድር የመክፈያ ጊዜው ከጫፍ መድረሱ ሲገልፅ ቆይቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም የከሰም ስኳር ፋብሪካም ተመሳሳይ የሸንኮራ አገዳ ምርት አጋጥሞት እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን፣ በ2009 አም 1.4 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ያመርታል ተብሎ ቢጠበቅም ችግሩ ጫና ማሳደሩ ተመልክቷል።

የስኳር ኮርፖሬሽን ለሸንኮራ አገዳው አለመኖርና ለፋብሪካው ስራ አለመጀመር የግንባታዎች መዘግየት በምክንያት አስቀምጧል።

በኮርፖሬሽን የስታቴጂካዊ ድጋፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ በዛብህ ገብረየስ የሸንኮራ አገዳ ምርት ለፋብሪካዎች ለማድረስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል። ይሁንና ሃላፊው በተንዳሆን ፋብሪካ ስራ ላይ ለሌሉ ሰዎች እየተከፈለ ስላለው ደመወዝ የሰጡት ምላሽ የሌለ ሲሆን፣ የፋብሪካዎቹ ግንባታ መጓተትና ተጨማሪ የበጀት ወጪ በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ኪሳራ ማስከተላቸው ይነገራል።

መንግስት ሃገሪቱ ስኳር ላኪ ያደርጓታል ያላቸውን 10 የስኳር ፋብርካዎች ግንባታ ከአመታት በፊት ለማስጀመር ከህንድና የቻይና መንግስታት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ብድር መስሰዱን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን አብዛኛዎቹን የስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ ለማከናወን በመንግስት ሃላሃፊነት እንደተሰጠው ለመረዳት ተችሏል።