ሰኔ ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ዘጋርድያን እንደዘገበው የተመድ የሰብአዊ መብቶች ካውንስል፣ ኢትዮጵያ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን፣ በአስቸኳይ አስፈላጊውን ካሳ በመክፈል እንድትለቃቸው ጠይቋል።
የእስረኞችን ጉዳይ የሚከታተለው የተመድ የሰብአዊ መብት ካውንስል በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ላይ በጭካኔ የተሞላ አካላዊ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንደተፈጸሙባቸው የሚያትቱ ተጨባጭ ማስረጃዎች እንዳሉት ለኢህአዴግ መንግስት በላከው 8 ገጽ ደብዳቤ ላይ ማስፈሩን ጋዜጣው ዘግቧል።
በሪፕሪቭ የህግ ክፍል ሃላፊ የሆኑት ማያ ፎአ የብሪቲሽ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አቶ አንዳርጋቸው ከእስር እንዲፈቱ አለመጠየቁን ተችተው፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አቶ አንዳርጋቸውን መፈታት መጠየቁ ትክክለኛ ነው ብለዋል።
የሪድሬስ የሰብአዊ መብት ድርጅት ሃላፊ ኬቪን ላዩ በበኩላቸው የዩናይትድ ኪንግደም መንግስት በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ላይ እየሆነ ባለው ነገር ቁጣውን መግለጽና ጠንካራ አቋም መያዝ አለበት ብለዋል።