ሐምሌ ፳፩(ሃያ አንድ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-አካባቢውን ጎብኝተው የተመለሱት የተመድ ዋና ጸሃፊ ባንኪ ሙን በጋዛ ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ መከሰቱን ጠቅሰዋል፡፡
ሁለቱም ተፋላሚ ሃይሎች ጦርነቱን እንዲያቆሙ በሰብአዊነት ስም እጠይቃለሁ በማለት ዋጻ ጸሃፊው ተናግረዋል።
የኢድ አል ፈጥርን በአል ምክንያት በማድረግ ሁለቱም ሃይሎች ተኩስ እንዲያቆሙ አለማቀፍ ማህበረሰቡ የጠየቀ ሲሆን፣ ሃማስ የተኩስ ማቆም ስምምነቱን በመጣስ በእስራኤል
ላይ ተወንጫፊ ሚሳኤሎችን መተኮሱ ታውቋል። ሃማስ ፣ እስራኤል ጋዛን ለቃ ካልወጠች እንዲሁም የእስራኤል ከበባ ካላቆመ በስተቀር ትግሉን እንደሚቀጥል አስጠንቅቋል።
እስራኤል በበኩሏ ሃማስ ውስጥ ለውስጥ የቆፈራቸውን መተላለፊያ ጉድጓዶች ለማውደም ሲባል በጋዛ እንደምትቆይ ግልጽ አድርጋለች።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ሁለቱ ሃይሎች በአስቸኳይ ተኩስ እንዲያቆሙ አዟል። ሁለቱም ሃይሎች የጸጥታው ምክር ቤት ያወጣውን መግለጫ ተችተውታል።
በእስካሁኑ ጦርነት ከ1 ሺ 40 በላይ ፍልስጤማውያን ሲገደሉ በእስረኤል ወገን ደግሞ 47 ሰዎች ተገድለዋል። እስራኤል 47 ወታደሮቿ ሲገደሉ፣ ከሃማስ ወገን ምን ያክል
ወታደሮች እንደሞቱ ቁጥሩ በውል አልታወቀም።