የካቲት ፲፬ ( አሥራ አራት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- እርዳታው በምስራቅ እና ደቡባዊ ኢትዮጵያ በድርቅ ተጎጂ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን ዜጎችን ሕይወት ለመታደግ ይውላል ተብሏል። ከ 5.6 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ውስጥ 785 ሽህ የሚሆኑት ለከፍተኛ ረሃብ የተጋለጡ መሆናቸውን ተመድ በሪፖርቱ ጠቅሷል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ቀውስ አስተባባሪ ኮሚቴ ሃላፊ ስቴፋን ኦብሪን ፣ በድርቁ ምክንያት በተለይ በምስራቅ ኢትዮጵያ የሚኖሩ ዜጎች ለከፍተኛ ርሃብ እና የውሃ ጥም ተጋላጭ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ይህም እርዳታ ተመድ ከድንገተኛ የአደጋ መከላከያ ፈንዱ የለገሰው ረድኤት ነው ብለዋል። ስቴፋን ኦብሪን ” በስፍራው ተገኝቼ እንዳየሁት ድርቁ በቤት እንስሳት ላይ እና በነዋሪዎች ሕይወት ላይ ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ ፈጥሯል። የነዋሪዎችን ሕይወት ለመታደግ ዛሬውኑ አፍጣኝ እርምጃ መውሰድ አለብን። ጊዜ ባባከንን ቁጥር የሰው ሕይወት ይጠፋል። የሰው ህይወት ከመጥፋቱ በፊት ባፋጣኝ ልንታደጋቸው ይገባል።” ሲሉ አክለዋል።
በኦጋዴን አካባቢ የሚኖሩ አርብቶ አደሮች ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ ባለመጣሉ ግጦሽ ፍለጋ ከመኖሪያ ቤታቸው እየፈለሱ መሆኑም በሪፖርቱ ተጠቅሷል። በአዱሱ ዓመት እ.ኤ.አ. 2017 በኢትዮጵያ እና በጎረቤት አገራት የርሃቡ አድማስ እየሰፋ ይመጣል ሲል ተመድ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። ባለፈው ዓመት ብቻ 47 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ለኢትዮጵያ እርዳታ የዋለ ሲሆን፣ ይህ ድንገተኛ የ8.5 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ልገሳም በቂ አይደለም ሲል ሪሊፍ ዌብ ዘግቧል።