የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሃላፊ ኢትዮጵያን ሊጎበኙ መሆኑ ተገለጸ

ኢሳት (ሚያዚያ 20 ፥ 2009)

በኢትዮጵያ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እና ግድያዎችን ለመመርመር ጥያቄ ሲያቀርብ የቆየው የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሃላፊ በኢትዮጵያ ጉብኝት ሊያደርጉ መሆኑ ተገለጸ።

የኮሚሽኑ ሃላፊ ዘይድ ራድ አል-ሁሴን በቀጣዩ ሳምንት ከሚያዚያ 24 እስከ 26 ፥2009 አም ድረስ በአዲስ አበባ ቆይታ እንደሚኖራቸው ኮሚሽኑ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የኮሚሽኑ ሃላፊ ራድ አል-ሁሴን በሃገሪቱ በተለይ በኦሮሚያ ክልል ለአንድ አመት ያህል ከዘለቀው ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተገናኘ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ከመጠን ያለፉ የሃይል ዕርምጃን ወስደዋል ሲሉ ተቃውሞ ማቅረባቸው ይታወሳል።

ተፈጽሟል የተባለው የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ግድያ በኮሚሽኑ እንዲሁም በሌሎች አለም አቀፍ ገለልተኛ ተቋማት በኩል ምርመራ መካሄድ እንዳለበት ሲያሳስብ ቆይቷል።

የአውሮፓ ህብረት አሜሪካና በርካታ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ይኸው ምርመራ መካሄድ እንዳለበት አሳስበዋል። ይሁንና መንግስት ጥያቄውን እንደማይቀበል በመግለጽ፣ ምርመራው በመንግስት እንደሚካሄድ ሲገልጽ መቆየቱ አይዘነጋም።

ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በጉዳዩ ዙሪያ ያካሄደውን ጥናት አስመልክቶ ባወጣው ሪፖርት 669 ሰዎች መገደላቸውን ይፋ አድርጓል።

የኮሚሽኑ ሪፖርት ከሃምሌ 2008 እስከ መስከረም 2009 አም ያለውን ጊዜ ብቻ የሸፈነ ሲሆን፣ መንግስት ከጥናቱ በተካሄደው ከሶስት ወር በፊት 113 ሰዎች መገደላቸውን ገልጾ እንደነበር የሚታወስ ነው።

ይሁንና አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት በመንግስት የተካሄደው ጥናት በገለልተኛ አካል ምርመራ ቢካሄድበት ውጤቱ ተአማኒነት እንደሚኖረው ይገልጻሉ።

በቀጣዩ ሳምነት በአዲስ አበባ የሶስት ቀን ጉብኝት የሚያደርጉት የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሃላፊ በሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ዙሪያ ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር ምክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

ኮሚሽነሩ ዘይድ ከአፍሪካ ህብረት ሃላፊዎች እንዲሁም ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር ከሰብዓዊ መብት ጋር በተገናኘ ሰፊ ውይይት እንደሚያካሄዱም ታውቋል።

የጉብኝታቸውን መጠናቀቅ ተከትሎም ኮሚሽኑ የፌታችን ሃሙስ ለጋዜጠኞች መግለጫን እንደሚሰጡም ለመረዳት ተችሏል።

በኦሮሚያ ክልል ለአንድ አመት ያህል በዘለቀውና በአማራ ክልል በቀጠለው ህዝባዊ ተቃውሞ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውን የተለያዩ አካላት ሲገልጹ ቆይተዋል።

ተቃውሞን ተከትሎ በተካሄደ ዘመቻ ከ24ሺ የሚበልጡ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ወደ አምስት ሺ አካባቢ የሚሆኑት ክስ እንደሚመሰረትባቸው ተገልጿል።