ኀዳር ፲፮ (አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ድርጅቱ ድርቁ እያስከተለ ያለውን ጉዳትና የደቀነውን ፈተና ወደ ተለያዩ ቦታዎች በመዟዟር በፎቶ ግራፍ በማስደገፍ አቅርቧል።
በሰሜን ወሎ ዳውንት ወረዳ የሚኖሩት አርሶአደርን፣ የስንዴ ማሳቸው በዝናብ እጥረት የተነሳ ደርቆባቸው ሃሳብ ገብቷቸው ይታያሉ
በጊዳን፣ ዳውንት፣ አበርጌሌ ወረዳዎች የጤፍ፣ የስንዴ፣ የዳጉሳና የማሽላ ማሳዎች በዝናብ እጥረት ምክንያት ደርቀው መሬቱም ተሰነጣጥቆ ይታያል።
በአፋር ፋንቲ ዞን ያሎ ወረዳ እንዲሁም ጋቢ ዞን ዱልሳ ወረዳ መሬቱ ሙሉ በሙሉ ደርቆ የሚታይ ሲሆን፣ በአካባቢው የነፈሰው ንፋስም የትምህርት ቤቱን ጣራ ነቅሎታል። በትግራይ ጎንካ ቀበሌ እንዲሁ ለእርዳታ የተመዘገቡ ሰዎች ከተመድ ሰራተኞች ጋር ሲወያዩ የሚያሳይ ፎቶ ድርጀቱ ለቋል።
መንግስታዊው ሄራልድ ጋዜጣ በአርሲ ዞን ዶዶታ ወረዳ ከ60 ሺ በላይ ሰዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንዲሰጣቸው መጠየቃቸውን ዘግቧል። በአንድንድ አካባቢዎች መግብ መከፋፈል ቢጀምርም፣ በዶዶታ 62 ሺ ህዝብ አስቸኳይ እርዳታ በፍጥነት ካልቀረበለት ህይወቱ አደጋ ውስጥ ይወድቃል። በዚሁ ወረዳ በምግብ ዋስትና ታቅፈው የነበሩ 5 ሺ 297 ሰዎችም የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የወረዳው የአደጋ እና ዝግጁነት ኮሚሽን ተወካይ ተናግሯል።
ለከብቶች መኖ ባለመቅረቡም 77 ሺ የቤት እንስሳት ሊያልቁ ይችላሉ፣ አንዳንድ ገበሬዎች እንስሶቻቸው እየሞቱባቸው መሆኑንም ተናግረዋል። አንድ ሰው በወር 15 ኪሎ ዱቄት እየተሰጠው መሆኑንም ጋዜጣው ዘግቧል።የርሃቡ መጠን ከዚህም የከፋ እንደሚሆን ተወካዩ ስጋታቸው ገልጸዋል።
በአርሶ ዞን ብቻ ከዚህ ቀደም አምራች ከሚባሉት ወረዳዎች ውስጥ 13ቱ በከፍተኛ ድርቅ ተጠቅተዋል።ጋዜጣው እንደዘገበው ከዚህ ቀደም በከፍተኛ ምርታቸው የሚታወቁት ወረዳዎች አሁን ምድረበዳ ሆነዋል። ቀበሌዎች በሙሉ የምግብ እርዳታ ጠባቂዎች ሆነዋል። በሌላ በኩል ደግሞ በሚሊዮን የሚቀጠሩ ዜጎች በተራቡበት በዚህ አስከፊ ወቅት ብአዴን የተባለው የኢህአዴግ ድርጅት የፊታችን እሁድ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ከፍተኛ ግብዣ አዘጋጅቷል።