ኢሳት (ሰኔ 3 ፥ 2008)
በቅርቡ በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች ተቀሰቀሶ ለበርካታ ሰዎች ሞት ምክንያት የነበረው አጣዳፊ የተቅማጥ በሽታ በኦሮሚያና ሶማሊያ ክልል በድጋሚ በወረርሽን መልክ ተቀሰቀሰ።
በሁለቱ ክልሎች በሚገኝ በርካታ ዞኖች በመሰራጨት ላይ ያለው በሽታ ለመቆጣጠር ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት አፋጣኝ ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በድርቁ ዙሪያ ይፋ ባደረገው ሪፖርት መልክቷል።
በቅርቡ በሁለቱ ክልሎች ተከስቶ በነበረው በዚሁ በሽታ 14 ሰዎች መሞታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ወደ ሁለት ሺ የሚጠጉ ሰዎችም በወረርሽኙ ተይዘው የህክምና ድጋፍ እንዲያገኙ ርብርብ ሲደረግ መቆየቱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አውስቷል።
በሶማሌ ክልል የሚገኘው የዶሎ ባይ ወረዳ የአጣዳፊ ተቅማት ወረርሽኙ በአዲስ መልክ ስርጭቱን የጀመረበት አካባቢ መሆኑን የገለጸው ድርጅቱ ወረርሽኙ ወደ አጎራባች ወረዳዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊሰራጭ የሚችል በመሆኑ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ ጥሪውን አቅርቧል።
ይኸው ወረርሽኝ በአሁኑ ወቅት በስደስት የኦሮሞያ ዞኖች በመዛመት ላይ ሲሆን የበሽታው ስርጭት በርካታ ወረዳዎችን ያደርሳል ተብሎ ስጋት መኖሩን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ካወጣው ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል።
በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች ያለው የውሃ እጦት ነዋሪዎች ንጽህናቸው ያልጠተበቀ ውሃን እንዲጠቀሙ በማስገደዱ ምክንያት በሽታው ዳግም ሊከሰት መቻሉ ታውቋል።
ባለፈው ወር የደቡብ ክልል ጨምሮ በተከሰተው በዚሁ ወረርሽኝ በትንሹ 19 ሰዎች መሞታቸውንና ወደ ሁለት ሺ የሚጠጉ ደግሞ በበሽታው ተይዘው መቆየታቸውን ድርጅቱ አመልክቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በደቡብ ክልል ኦሞ ዞን በተከሰተው የቢጫ ወባ በሽታ ከ20 የሚበልጡ ሰዎች ለህመም መዳረጋቸውንና በትንሹ አምስት ነዋሪዎች መሞታቸው ታውቋል።
የበሽታው መከሰት አሳሳቢ በመሆኑም ከታማሚ ሰዎች የተወሰደ ናሙና በአለም ጤና ድርጅት እውቅና ባላቸው የህክምና ተቋማት ምርመራ እንዲካሄድበት መላኩን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገልጿል።
በድርቅ በተጎዱ ስድስት ክልሎች የተላላፊ በሽታዎች ስርጭት አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱ ድርጅቱ በሪፖርቱ አመልክቷል።