ጥር ፳፯(ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የ9ኙ ፓርቲዎች በጠራው የአዳር ሰልፍ ታስረው የነበሩት የመቶ አለቃ ተሰማ ወንድሙ በእስር ቤት ሳሉ በደረሰባቸው ድብደባና መድሀኒት ክልከላ ህይወታቸው ማለፉን ነገረ-ኢትዮጰያ ዘገበ
የመላው አማራ አንድነት ድርጅት ምክትል ጸሀፊ የሆኑት መቶ አለቃ ተሰማ ወንድሙ የህዳር 27/28 የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር በጠራው የአዳር ሰልፍ ላይ ነው ክፉኛ የተደበደቡት።
የስኳር ህመምተኛ የሆኑት የመአህድ ምክትል ጸሀፊ ከደረሰባቸው የከፋ ድብደባ ባሻገርም ወደ እስር ቤት ተወስደው ለሶስት ተከታታይ ቀናት መድሃኒት እንዳይገባላቸው መከልከላቸው ለከፋ ህመም እንደዳረጋቸው ተገልጿል።
በድብዳባና በእስር ቤት መድሀኒት በመከልከላቸው ክፉኛ የታመሙት መቶ አለቃ ተሰማ ወንድሙ፤ ከእስር ከተፈቱበት እለት ጀምሮ ለሁለት ወር በዘውዲቱ ሆስፒታል ከቆዩ በኋላ በዛሬው ዕለት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡
የስኳር ህመምተኛው መቶ አለቃ ተሰማ ወንድሙ በአዳሩ ሰላማዊ ሰልፍ ወቅት ከደረሰባቸው ድብደባ ባሻገር ለአምስት ቀናት ቀዝቃዛና ጨለማ ቤት ውስጥ ታስረው ቆይተዋል፡፡
የመቶ አለቃ ተሰማ ወንድሙ የቀብር ስነስርዓት ዛሬ ጥር 27/2007 ዓ.ም በቦሌ ሚካኤል እንደሚፈጸም ለማወቅ ተችሏል፡